መነሻቸውን ያልረሱት ኮከቦች

0
194

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሳዲዮ ማኔ ለሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በክለብ ደረጃ ደግሞ ለሳዑዲው አልናስር ይጫወታል። ከአልናስር በፊት በባየር ሙኒክ እና በሊቨርፑል ተጫውቷል። በተለይ በሊቨርፑል የነበረው ብቃት ለክለቡ ውጤታማነት ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ አድርጎታል።
ማኔ ከተጫዋችነቱ ባለፈም በበጎ ተግባራቱ የሚቀናበት ነው። በተወለደበት አካባቢ ማኅበረሰብም ዘንድ “በጎ አሳቢ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።

የ32 ዓመቱ ማኔ 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዩሮ በዓመት ይከፈለዋል። እንደ አውሮፖውያኑ ዘመን በ2021 ማኔ ሴኔጋል ውስጥ ማኅበረሰቡን ለመጥቀም በማሰብ የሕዝብ ሆስፒታል ለመገንባት ወሰነ። ውሳኔውንም በተግባር ለማስፈጸም 500 ሺህ ዩሮ ለገሰ። ማኔ ይህን የወሰነው የአባቱን ሞት ተከትሎ እንደኾነ ነው የሚነገረው።

ማኔ አባቱ በሕክምና እጦት መሞታቸውን ሲያስተውል ይህ ችግር በሌሎችም እንዳይደገም በማሰብ ተግባሩን ለመፈጸም ተነሳ፤ አደርገውም። ሳዲዮ ማኔ ዓለምን መለወጥ ይቻላል የሚል እሳቤ ያለው የኳሱ ዓለም ሰው ሲኾን ይህን ለመከወን ከእያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ እና የተግባር ሰውነት እንደሚነሳ ነው የሚናገረው።

የተግባር ሰው እንደኾነ የሚነገርለት ማኔ አዲስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በትውልድ መንደሩ ባምባሊ ውስጥ ሌሎች ሥራዎችንም መሥራት እንደቻለ ነው የሕይወት ታሪኩ የሚያስረዳው። ማኔ የኮሮና ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት ወቅትም በሽታውን ለመከላከል ለሀገሩ እስከ 40 ሺህ ፓውንድ ለሴኔጋል መንግሥት መስጠቱም ይነገርለታል።

በአፍሪካ ውስጥ ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ መሠራት እንዳለበት ከሚያምኑ እና ከሚደግፉ ሰዎች መካከልም ማኔ የፊት መሥመሩን ይይዛል። ሌላው ዓለምን መቀየር እንደሚቻል በማሰብ እየተንቀሳቀሰ ያለው የኮትዲቯር የቁርጥ ቀን ልጅ ዲዴ ድሮግባ ነው።
ድሮግባ በኳሱ ዓለም ከሀገሩ አልፎ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለቼልሲ በመጫወት አፍሪካን ያኮራ አሁን ላይ ራሱን ከኳሱ ያገለለ ሰው ነው።

ዲዴ ድሮግባ ዓለምን ለመቀየር ከሰፈር መነሳት እንደሚያስፈልግ በማመን እየሠራ ያለ ድንቅ የኳሱ ዓለም ሰው ነው። ዲዴ ለሕዝብ በማሰብ የተለያዩ የሚያነሳሱ አነቃቂ ሥራዎችን በመሥራትም ይታወቃል። የ46 ዓመቱ ድሮግባ እ.ኤ.አ. በ 2005 በወቅቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለነበረችው ሀገሩ ኮትዲቮር ሰላምን የሚያበረታታ ንግግር በማቅረብ ችግሩ በንግግር እንዲፈታ የራሱን ሚና ተጫውቷል።

የልጆች የመማር መብት የሚያበረታታ ዲዴር ድሮግባ ፋውንዴሽንን በመመሥረት አካባቢውን ለመቀየር የበኩሉን እየተወጣም ይገኛል። ፋውንዴሽኑ በኮቴዲቯር ወላጆቻቸውን ላጡ እና አቅመ ደካሞች ሕጻናት የትምህርት ቁሳቁሶችን እንዲያገኙ ማድረግ የቻለም ነው።

እ.ኤ.አ. በ 2018 ድሮግባ እና ሌሎች የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተገናኝተው 15 ሚሊዮን ዩሮ በመሰረተ ልማት፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና በአፍሪካ የንግድ ጅምር ዕርዳታ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሠራው ሥራ ድሮግባን የተግባር ሰው ያስባለው ክስተትም ኾኗል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here