የአበበ ቢቂላ መታሰቢያ የግማሽ ማራቶን ውድድር በጃፖን ተካሄደ።

0
207

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጃፓን ኢባራኪ ግዛት ካሳማ ከተማ የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ እና 19ኛው የካሳማ ከተማ የግማሽ ማራቶን ውድድር ተካሂዷል። ውድድሩ ትላንት መካሄዱን በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

ውድድሩን በአንደኝነት ላጠናቀቀው ተወዳዳሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ- ቶኪዮ- ናሪታ የደርሶ መልስ የአየር ቲኬት እንዲኹም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎችም የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክቷል። በጃፓን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዳባ ደበሌ የግማሽ ማራቶን ውድድሩን ማስጀመራቸውም ተጠቅሷል።

የጃፖን መንግሥት ይህን ውድድር በማዘጋጀቱ እና የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ በማድረጉ ምስጋና በማቅረብ መሰል ውድድሮች ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በስፖርቱ ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ሚናው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። በከተማው የሚገኝ የስፖርት ቁሳቁሶችን የሚያመርት ኩባንያ ላደረገው የቅርጫት ኳስ ድጋፍም አመስግነዋል። የካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ በበኩላቸው ከተማው ከኤምባሲው ጋር እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በቀጣይ ዓመት የሚደረገው የ20ኛ ዓመት መታሰቢያ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ ለማዘጋጀት እንደሚሠሩ መናገራቸውም ተገልጿል።

እንዲኹም ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ጉድኝት በመመስረት በትብብር መሥራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። በከተማዋ ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በቋሚነት እንዲታወስ በስሙ ጎዳ እና ወይም ፓርክ እንዲሰየምለት በአምባሳደር ዳባ ደበሌ የቀረበውን ጥያቄ እንደተቀበሉት እና ከኤምባሲው ጋር ተባብሮ ቋሚ ማስታወሻ ለማኖር ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here