ባሕር ዳር ከተማ ወደ መሪነት ይበልጥ የሚያስጠጋውን ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ ያደርጋል።

0
211

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሲደረግ ባሕር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ። ባሕር ዳር ከተማዎች ከ10 ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፈው፣ በሁለቱ አቻ ተለያይተው እና በሦሥቱ በመሸነፍ 17 ነጥብ በመሠብሠብ መሪውን መቻልን ተከትለው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የጣና ሞገዶቹ የአጨዋወት ሥልታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ በመሄድ አሁን ላይ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በመኾኑም ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ መቻል ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአምስት መርሐ ግብሮች ሳይሸነፉ የዘለቁት ባሕር ዳር ከተማዎች የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሸነፍ ብቃታቸውን አሳይተዋል።

ይህም የዛሬውን ጨዋታ እንዲያሸንፉ ከፍተኛ ጉልበት እና የሥነ ልቦና ተነሳሽነት ይፈጥርላቸዋል ነው የተባለው። በተለይ የቡድኑ ከበረኛ እስከ ፊት መስመር አጥቂዎች የሚፈጥሩት ጥምረት ከጨዋታ ውበት እና ማራኪነት ባለፈ የድል ተነሳሽነቱን ከፍ አድርጎታል። በባሕር ዳር ከተማ በኩል ፍሬዘር ካሳ ከቅጣት ይመለሳል።

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅርብ ሳምንታት በተካሄዱ ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻል አሳይቷል። ይሁን እና ቡድኑ ከሠበሠባቸው ስመ ጥር ተጫዋቾች አኳያ በማጥቃቱ ረገድ ቀዝቅዟል። ለአብነትም በሦስት መርሐ ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ የአጥቂውን ክፍል ድክመት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ክዋሜ ፍሪምፓንግ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ውጭ ሲኾን በረከት ወልዴ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ኾኗል። ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 10 ጊዜ የተገናኙ ሲኾን ባሕር ዳር ከተማ ሦስት ጊዜ አሸንፏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት ድል ነስቷል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በሌላ በኩል ምሽት 1ሰዓት ሀድያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና እንደሚጫወቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር እና ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገጻቸው አስነብበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here