ተጠባቂው የባሕር ዳር ከተማ እና ንግድ ባንክ ጨዋታ ምሽት ይካሄዳል።

0
192

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታ ባሕር ዳር ከተማ እና ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። የጣና ሞገዶቹ 14 ነጥብ በመሠብሠብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከመሪው መቻል ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ለማጥበብም የዛሬውን ጠንካራ ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታቸው ነው።

ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በመቀሌ 70 እንደርታ በጊዜ ግብ ተቆጥሮበት እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ እጅ ላለመስጠት ያደረገው ትግል ነጥብ እንዲጋራ አግዞታል። ይሄም ለዛሬው ተጠባቂ መርሐ ግብር እንደሚያነሳሳው ይጠበቃል። የአምናው የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀሪ ጨዋታ በእጃቸው እያለ በስምንት ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘዋል። የመጨረሻ ጨዋታቸውንም ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ተጋርተዋል።

በዛሬው የምሽት አንድ ሰዓት ጨዋታ ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ ከባሕር ዳር ከተማ፣ ሱሌማን ሐሚድ እና ፉዓድ ፈረጃ ከንግድ ባንክ በተለያየ ምክንያት ጨዋታው ያልፋቸዋል። ቀን 10:00 ሰዓት በሚደረግ ጨዋታ ደግሞ አርባ ምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ። ባለፉት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ለማግኘት የተቸገረው ቡና ስምንት ነጥብ ነው እስካሁን የሠበሠበው። ደረጃው ደግሞ 15ኛ ነው።

አርባ ምንጭ ደግሞ በ1ዐ ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለፈው ጨዋታ በመቻል ተሸንፏል። ዛሬ ከሽንፈቱ ለማገገም በማሰብ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here