ባሕር ዳር: ጥር 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሊጉ የአስራ አንደኛ ሳምንት መርሐ ግብሩን ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጀምራል። ቀን 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ምሸት 12 ሰዓት የአማራ ክልሉ ተወካይ ባሕርዳር ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኛል፡፡
በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ የጣለው ባሕር ዳር ከተማ ከአስር ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፎ፣ በአራቱ አቻ ወጥቶ፣ በአንዱ ተሸንፎ እና በስድስት ንጹህ የግብ ክፍያ 19 ነጥብ በመያዝ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ካምፓኒ በድረ ገጹ አስታውቋል።
የጣና ሞገዶቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተመሳሳይ የሚባል ፈተና ገጥሟቸዋል፤ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ የግብ ክልላቸውን አጥረው የሚከላከሉ ቡድኖችን ነበር የገጠመው፡፡ ባሕር ዳር ከተማ በሁለቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችልም የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ግብ ማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል።
አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ እንዳመጣላቸው በአጨዋወት ስልታቸው ላይ ለውጥ አድርገው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ባሕርዳር ከተማ ከአደም አባስ ውጭ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም፡፡
የአሠልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን መያዝ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ከአስር ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፈው፣ በሦስቱ አቻ ወጥተው፣ በአራቱ ተሸንፈው እና በአንድ ንጹህ የግብ ክፍያ 12 ነጥብ በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከዚህ ቀደምም ጥሩ የነበረውን የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ማስቀጠል ችለዋል፡፡ እሳቸው ካደረጓቸው በሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አላቸው። ኾኖም ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ያለውን ውስንነት መቅረፍ አልቻሉም፡፡
ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረጉት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ወጥተዋል። ስለዚህ የቡድኑን የማጥቃት አጨዋወት የማስተካከል ሥራ የአሠልጣኝ ዘላለም ቀዳሚ ሥራ ይኾናል ተብሎ ይታመናል። በሲዳማ ቡና በኩል በጉዳትም ኾነ በቅጣት ጨዋታ የሚያልፈው ተጫዋች የለም። ባሕርዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ምሽት 12 ሰዓት የሚያደርጉትን ጨዋታ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል፡፡ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሻረው ጌታቸው ረዳት ዳኞች ናቸው፡፡ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል፡፡
ቀን 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና የሚያገናኘው ጨዋታ የ11ኛው ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ይኾናል። ከሰርቢያዊው አሠልጣኝ ኒኮላ ኮቫዞቪች ጋር ውል ያቋረጠው ኢትዮጵያ ቡና አሠልጣኝ ነፃነት ክብሬን ከቀጠረ በኃላ ባደረጋቸው የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቧል። ባለፈው ሳምንት ግን ባልተጠበቀ መልኩ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ከአስር ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ፣ በሦስቱ አቻ ወጥቶ፣ በሦስቱ ተሸንፎ በ15 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና የግብ እድሎችን ከመፍጠር አንፃር ያለበትን ውስንነት አርሞ መግባት ይጠበቅበታል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ አማካያቸውን አማኑኤል ዮሀንስን በጉዳት አያሰልፉም፡፡ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅም በግል ጉዳይ ምክንያት ለዚህ ጨዋታ አይደርስም ተብሏል።
እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ዋና አሠልጣኙን አሰናብቶ ምክትላቸውን በጊዜያዊነት ወደ ዋና አሠልጣኝነት ያመጣው ሀዲያ ሆሳዕና ፋሲል ከነማን እና አዳማ ከተማን ማሸነፍ ችሏል፡፡
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንትም ከጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብ በመጋራት ከአስር ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ፣ በስድስቱ አቻ ወጥቶ፣ በሁለቱ ተሸንፎ ነጥቡን ወደ 12 በማሳደግ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሀዲያ ሆሳዕና ዛሬ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ እንደ ሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ በሀድያ ሆሳዕና በኩል በአባቱ ሞት ምክንያት ከቡድኑ ጋር ዳዋ ሆቴሳ በዛሬው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡ ሔኖክ አርፊጮ ፣ ብሩክ ማርቆስ እና ካሌብ በየነም በጉዳት እንደማይኖሩ ተገልጿል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል፡፡ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል፡፡ ተካልኝ ለማ አራተኛ ዳኛ ኾነው ተሰይመዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!