በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

0
160

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በድሬ ዳዋ ስታዲየም ዛሬ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድን 10 ሰዓት ላይ በሚያደርጉት ጨዋታ የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር ይጀመራል፡፡ ኢትዮጵያ መድን ከስምንት ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ፣ በሦስቱ አቻ ወጥቶ እና በአንዱ ተረትቶ በ13 ነጥብ ስድስተኛ ላይ ይገኛል፡፡ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደረጃውን ከፍ ማድረግ ያስችለዋል፡፡

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ አምስት ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ነጥብ ብቻ በመያዝ 15ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ በባለፈው የውድድር ዓመት ሊጉን በበላይነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተቀዛቀዘው የዘንድሮ አጀማመሩ ተላቆ ወደሚታወቅበት ውጤታማነት ለመምጣት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል። ኢትዮጵያ መድንን እንደመግጠሙ በተሻለ የመከላከል አቅም መቅረብም ይጠበቅበታል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች 22 ጊዜ የተገናኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሥር፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ሦስት ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ በዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬ ዳዋ ከተማ የሚጫወቱ ይኾናሉ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ16 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በስድስት ድሬ ዳዋ ከተማ ደግሞ በአራት ጨዋታዎች አሸንፈዋል፡፡ በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ፕሪምየር ሊጉን መቻል በ15 ነጥብ ሲመራው፣ ወላይታ ድቻ በ14 ነጥብ በሁለተኛነት ይከተላል፡፡ ባሕር ዳር ከተማ በ13 ነጥብ ሦስተኛ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር ድረ ገጽ መረጃ ስሁል ሽረ፣ ሐዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወራጅ ቀጣና ላይ ተቀምጠዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here