ጎንደር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሥልጠናው የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ጋር በመተባበር የሚሰጡት ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በጎንደር ከተማ ከስድስት ዓመት እስከ 12 ዓመት እግር ኳስ ለሚያሠለጥኑ የ”ዲ” ላይሰንስ የአሠልጣኞች ሥልጠና ነው በጎንደር ከተማ እየሠጠ የሚገኘው።
በሥልጠናው ከማዕከላዊ ጎንደር፣ ከምዕራብ ጎንደር፣ ከሰሜን ጎንደር እና ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተወጣጡ 60 አሠልጣኞች እየተሳተፋ ይገኛሉ።
ሥልጠናው በየትኛውም የአፍሪካ አህጉር ውስጥ ለማሠልጠን ብቁ የሚያደርጋቸው መኾኑን የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን የሴቶች እግር ኳስ ልማት ኀላፊ እና የካፍ ኢንስትራክተር በኃይሏ ዘለቀ ተናግረዋል። የሥልጠናው ተካፋዮች ዓለም አቀፍ የስፓርት ሳይንስ የደረሰበትን ምጥቀት መሠረት በማድረግ በንድፈ ሃሳብ የታገዘ ክህሎታቸውን እንደሚያሳድግላቸው ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በአራት የስፖርት አይነቶች ላይ የአሠልጣኞች ሥልጠና መስጠት መቻሉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማሩ መሐመድ ተናግረዋል። የአሠልጣኞችን ብቃት ለማሳደግ በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን የገለጹት ኀላፊው አሁን የሚሰጠው ሥልጠና ለታዳጊ ሠልጣኞችም ዕድል የሚሰጥ መኾኑን አስረድተዋል።
በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ያለው የ”ዲ” ላይሰንስ የእግር ኳስ የአሠልጣኞች ሥልጠና ለ11 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መኾኑም ታውቋል።
ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!