ሦስተኛው ባለታሪክ

0
151

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2024/ 2025 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ36 ቡድኖች በዙር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህ ውድድር ከጨዋታ ጨዋታ የተለያዩ ታሪካዊ ኹነቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡ የስፔኑ ኀያል ቡድን ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ብረስት ጋር ትናንት በተደረገው ጨዋታ ቡድኑን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2022 የተቀላቀለው ፖላንዳዊው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በ10 ኛው እና ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

ይህም ተጫዋች በሻምፒዮንስ ሊጉ በ125 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛት 101 በማድረስ ድንቅ አጥቂነቱን አስመስክሯል፡፡ በትናንቱ ጨዋታ ቡድኑ ባርሴሎናም ብሬስትን 3ለ0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በመኾኑም ከአምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ተሸንፎ በአራቱ አሸንፎ በ12 ነጥብ ከመሪው ኢንተር ሚላን በአንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በሁለተኛነት ተቀምጧል፡፡

ይህን ተከትሎም ተጫዋቹ ለሞቪስታር የዜና አውታር በሰጠው አስተያየት “በሻምፒዮንስ ሊግ የዚህ አስደናቂ ክብረ ወሰን ባለቤት መኾን እችላለሁ ብየ አልጠበቅሁም ነበር፡፡ ከሊዮኔል ሜሲ እና ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ጥሩ ወዳጅነት አለኝ። የክብረ ወሰኑ ተጋሪ በመኾኔ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል ተናግሯል።

ሌዋንዶውስኪ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2011/12 ጀምሮ በሁሉም የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ተሰልፎ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህ የ36 ዓመቱ ተጫዋች በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ100 በላይ ግቦችን በማለፍ ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ የያዙትን ክብረ ወሰን የተጋራ ሦስተኛው ተጫዋች ለመኾን አስችሎታል፡፡

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ በ183 ጨዋታዎች ተሰልፎ 140 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ በባርሴሎና እና ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን በ163 ጨዋታዎች ተሰልፎ 129 ግቦችን መረብ ላይ በማሳረፍ የክብረ ወሰን ባለቤት መኾን ችሏል፡፡

“ከ10 እስከ 14 ዓመቴ እያለሁ አሌክሳንድሮ ዴል ፒሮ ለእኔ ምርጥ ተጫዋች ነበር” የሚለው ሌዋንዶውስኪ እንደ ቲዬሪ ሄንሪ መጫወት ይፈልግ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ አርዓያዎቼን እያሰብኩ በመጫወቴ ለስኬት በቅቻለሁም ብሏል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here