በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

0
217

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2024/2025ቱ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 36 ቡድኖች በዙር እየተፎካከሩበት ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም ቡድኖቹ አራት ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ የእንግሊዙ ሊቨርፑል ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ12 ነጥብ በፊት አውራሪነት ተቀምጧል፡፡

በዛሬው የአምስተኛ ዙር መርሐ ግብር ዘጠኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። የጀርመኑ ባየርን ሙኒክ የፈረንሳዩን ፒኤስጂ እንዲኹም የፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን የእንግሊዙን አርሰናል የሚጋብዙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየርን ሙኒክ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ እና በሁለቱ ተሸንፎ በስድስት ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ቡንደስሊጋውን በ29 ነጥብ እየመራ እንደሚገኝ ልብ ይሏል፡፡

የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንት ዤርሜን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ ተለያይቶ እና በሁለቱ ደግሞ ተሸንፎ በአራት ነጥብም 27ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እስካኹን በ13 መደበኛ ጨዋታዎች ተገናኝተው ባየርን ሙኒክ በሰባት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ፒኤስጂ በአንጻሩ ያሸነፈው በስድስት ጨዋታዎች ነው፡፡

ሁለቱ ቡድኖች የየሀገራቸውን ሊግ በመምራት ላይም ይገኛሉ፡፡ ታዲያ ካላቸው ወቅታዊ አቋም አንጻር ጨዋታዉ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ይደረጋል፡፡

ሌላው ስፖርቲንግ ሊዝበን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው፡፡ የፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ በሦስቱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ ተለያየቶ አሥር ነጥብ በመያዝ በሁለተኛነት ተቀምጧል፡፡

የእንግሊዙ አርሰናል በበኩሉ በሁለት ጨዋታ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ ተለያቶ እና በአንድ ጨዋታ ተረትቶ በሰባት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል፡፡

በአርሰናል በኩል በጡንቻ ህመም ከሜዳ ርቆ የቆየው ስኮትላንዳዊ የግራ መሥመር ተከላካይ ኬራን ቴርኒ በቡድኑ ተካቷል፡፡ ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት በኢስታዲዮ ጆዜ አልቫላዴ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

ሌሎች ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ስሎቫን ብራቲስላቫ ከ ኤሲሚላን እንዲኺም የቼክ ሪፐብሊኩ ስፓርታ ፕራግ ከ አትሌቲኮ ማድሪድ ይጫወታሉ፡፡

ምሽት 5 ሰዓት ላይ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ብረስት፣ የጀርመኑ ባየር ሊቨርኩሰን ከኦስትሪያው ሬድ ቡል ሳልዝበርግ፣ ኢንተር ሚላን ከአርቢ ሌብዚግ፣ ማንቸስተር ሲቲ ከኔዘርላንዱ ፌይኖርድ እንዲኹም የሲዊዘርላንዱ ያንግ ቦይስ ከጣልያኑ አታላንታ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይኾናሉ፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here