በአሞሪም የመጀመሪያ ጨዋታ ምን ለውጥ ታየ?

0
233

ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከገናናው ሰው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጡረታ መውጣት በኋላ ሁነኛ ሰው ያላገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በቅርቡ ተስፋ የተጣለባቸውን ፖርቹጋላዊ አሠልጣኝ መሾሙ ይታወሳል፡፡ በ39 ዓመታቸው እንደ እሳት የሚፋጀውን የማንቸስተር ዩናይትድ ወንበር የተረከቡት ፖርቱጋላዊው ሩበን አሞሪም ታላቅ ተስፋ ተጥሎባቸው በዩናይትድ ቤት ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ ከሌሎች ክለቦች የቀረበላቸውን ጥያቄዎች ጀሮ ዳባ ልበስ ብለው ለማንቸስተር ዩናይትድ ጀሯቸውን ያዘነበሉት አሠልጣኙ በአዲሱ ኀላፊነታቸው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን መርተዋል፡፡

በሀገራቸው ፖርቱጋል ስፖርቲንግ ሊዝበንን አስደናቂ ክለብ አድርገው የገነቡት ወጣቱ አሠልጣኝ ለማንቸስተር ዩናይትድም ሁነኛው ሰው ናቸው እየተባለ ነው፡፡ የመጪው ዘመን የአውሮፓ እግር ኳስ አልጋ ወራሽ እንደሚኾኑ ተስፋ የተጣለባቸው ሩበን አሞሪም ማንቸስተር ዩናይትድን እያሠለጠኑ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መርተዋል፡፡

ምን እንኳን በመጀመሪያ ጨዋታቸው አዲስ አዳጊውን ክለብ ኢፕሲውችን መርታት ባይችሉም በክለቡ ውስጥ አዲስ ነገር አሳይተዋል ተብሏል፡፡ ሩበን አሞሪም በማንቸስተር ዩናይትድ ለተጀመረው አዲስ አቢዮት የተመቻቹ፣ ቀስ በቀስ የራሳቸውን የእግር ኳስ እውቀት ከማንቸስተር ዩናይትድ ባሕል ጋር የሚያዛምዱ እና የሚያዋድዱ አሠልጣኝ እንደሚኾኑ ይጠበቃል፡፡

ትናንት አመሻሽ ወደ ፖርትማን ሮድ ስታዲዬም ተጉዘው ነጥብ ተጋርተው ከተመለሱ በኋላ ስለ አሞሪም እና ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ እግር ኳስ አስተያየቶች እየቀረቡ ነው፡፡ የቢቢሲ ስፖርት አምደኛው ዳኒ መርፊ በሩበን አሞሪም ስር የተለየ ማንቸስተር ዩናይትድን የተመለከትን መስሎ ይሰማኛል፤ ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ለመፍታት ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ናቸው ብሏል፡፡

በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት ከሁሉም ተጨዋቾች ጋር ተመሳሳይ ልምምድ ያልሠሩት አሞሪም ሁለት አይነት አሠለጣጠን እንዲጠቀሙ እንደተገደዱ ነው የተገለጸው፡፡ አሠልጣኙ ግን ተስፋ ሰጪ የጨዋታ ዘይቤዎችን አሳይተዋል ነው ያለው ዳኒ፡፡ ሦስት አራት ሦስት የአሰላለፍ ምርጫ ያላቸው አሠልጣኙ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ነጥብ ተጋርተው ቢወጡም ተጨዋቾች እንዲተገብሩት የፈለጉት አዲስ ተግባር እንደነበረ ነው አምደኛው የሚናገሩት፡፡

ተለዋዋጭ የአጨዋወት ዘይቤ ያላቸው አሠልጣኙ አዲስ ነገር አሳይተዋል ነው የሚሉት፡፡ በጨዋታው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች ሲያደርጓቸው ከነበሩት ጨዋታዎች በተለየ መልኩ በራስ መተማመን ያላቸው እና ደፋር ኾነው ታይተዋል ነው ያሉት፡፡ ኳስ ሲነጠቁ ግን ለተቃራኒ ቡድን የተመቹ ነበሩ ነው የሚሉት፡፡

የመስመር ተከላካዮችን የበለጠ ወደ ፊት እንዲቀርቡ እና እንዲያጠቁ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጠንካራ እና ጫና እንዲፈጥር ያደረጉበት መንገድ የተሻለ እንደነበር ነው የተነሳው፡፡ አሠልጣኙ ተጨዋቾች የተለያየ ሚና ይዘው እንዲጫወቱ ማድረጋቸው እና የተቃራኒ ቡድንን የአጨዋወት እንቅስቃሴ እየተመለከቱ ስልታቸውን መቀያየራቸው እግርኳሳዊ እውቀታቸው ከፍ ያለ እንደኾነ ነው አምደኛው የተገለጹት፡፡

ማንቸስተር ዩናይትድ በኤሬክ ቴን ሃግ ስር ከነበረበት ጊዜ በተለየ መልኩ ተለዋዋጭ የአጨዋወት ዘይቤ ማሳየቱን እና በማጥቃት በኩል የተሻለ ነበር ነው የሚሉት፡፡ ምን አልባትም ዩናይትድ አዲስ የተገበረው የአጨዋወት ቅርጽ እስኪለመድ ድረስ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡የማንቸሰተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ትናንት ከታየው ውጤት ማሻገር ባዩት ተስፋ ምክንያት ለአዲሱ አሠልጣኝ መዘመር መጀመራቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

ደጋፊዎቹ በቴን ሃግ የታየውን ደካማ ጎዞ አስተካክለው ውጤት እንዲያመጡላቸው ከሩበን አሞሪም ይፈልጋሉ፡፡ አሠልጣኙ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ውጤት ለደጋፊዎች አስደሳች እንዳልኾነ ተናግረዋል፡፡ ወደ ተሻለ ነገር ለመምጣት ፈተናዎች እንደሚጠብቋቸው እና ፈተናዎችን ማለፍ ግድ እንደሚልም አንስተዋል፡፡ አሠልጣኙ በክለቡ ውስጥ ብዙ ሊፈቷቸው እና ሊያስተካክሏቸው የሚገቡ ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተስፈኛው አሠልጣኝ አሞሪም አዲስ የአሰላለፍ እና የአጨዋወት ዘይቤያቸውን ለማላማድ በቂ ጊዜ እንዳልነበራቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ቀጣይ ለሚኖሯቸው ተከታታይ ጨዋታዎችም ለአሠልጣኙ እና ለቡድናቸው በቂ የመዘጋጃ ጊዜዎች የሉም ነው የተባለው፡፡ አሞሪም አዲሱን የአጨዋወት ስልታቸውን ለመተግበር ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች የተመለሱትን ተጨዋቾች በሚገባ መጠቀም እንደሚጠበቅባቸውም ተመላክቷል፡፡ ወደ ትክክለኛው የአጨዋወት ስልት እና ወደ ሚፈለገው ብቃት ለመምጣት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

ተስፈኛው አሠልጣኝ ጊዜ እያገኙ ሲሄዱ በዩናይትድ ቤት ጥሩ ሥራ እንደሚሠሩም ይጠበቃል፡፡ ትናንት ካስመዘገቡት ነጥብ ባሻገር የጀመሩትን ስልት እና ሊተገብሩት ያሰቡትን ማየት የተሻለ እንደኾነ ነው የተነገረው፡፡ በአንድ ጨዋታ ፍጹም የኾነ ቡድን መጠበቅ አይገባምና፡፡ ስካይ ስፖርት በዘገባው በማንቸስተር ዩናይትድ ያለው አዲስ መዋቅር ለአዲሱ አሠልጣኝ ትልቅ ተስፋ እና ዕድል ነው ብሏል፡፡

አኹን ያሉት ተጨዋቾች በተለያዩ አሠልጣኞች ጊዜ የተሰበሰቡ መኾናቸውን ያስታወሰው ስካይ ስፖርት ለሚተገብሩት አዲስ የአጨዋወት ዘይቤ አመቺ ሊኾኑ እንደማይችሉ ነው ያመላከተው፡፡ በሩበን አሞሪም ላይ ብሩህ ተስፋ አለ፣ ነገር ግን አፈጻጸሞች እና ውጤቶች ከተስፋው ጋር ካልተሻሻሉ ተስፋው በፍጥነት ይጠፋል ነው ያለው ስካይ ስፖርት፡፡

ማንም ሰው በእውነቱ አሞሪም ዩናይትድን በአጭር ጊዜ ውስጥ እውነተኛ ተፎካካሪ ያደርጉታል ብሎ የሚጠብቅ የለም፡፡ ምናልባት በመጀመሪያው የውድድር ዘመን የስኬት መለኪያ የሚኾን ማንነት ለመፍጠር የገቡት ቃል ነው የሚጠበቀው ብሏል ስካይ ስፖርት በዘገባው፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here