ባለሌላ መልኮች!

0
181

ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ስማቸው በጉልህ የሚጠሩ እግር ኳሰኞች ኳስ ከማንከባለል በቀር ሌላ ክህሎት የሌላቸው የሚመስለን ብዙዎች ነን። ነገር ግን ይሄንን እሳቤያችንን ውድቅ የሚያደርጉብን በርካታ ተጫዋቾች አሉ፡፡

በእርግጥ አብዛኞቹ የእግር ኳስ ተጫዋቾች እግር ኳስ ሁሉ ነገራቸው ቢኾንም ከኳሱ ባሻገር የሌሎች መክሊቶች ባለቤት ኾነውም ታይተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ባለ መንታ ተሰጥኦ ባለቤት የኾኑት እግር ኳሰኞች ድብቁን መክሊታቸውን በአደባባይ ስለማያሳዩን የምናውቅላቸው የሜዳ ሥራቸውን ብቻ ነው።
ቀደም ሲል በፉልሃም የአጥቂ አማካይነቱ የምናውቀው አሜሪካዊው ክሊንት ዴምሲ ከእግር ኳሱ ባሻገር ምርጥ ”ራፐር ” ወይም ዘፋኝ እንደኾነ ብዙዎቻችን አናውቅም።

ዴምሲ ከኔዘርላንዳዊው የአትሌቲኮ ማድሪድ አጥቂ ሜሚፊስ ዴፓይ ጋር በጋራ ራፕ በማድረግም ብዙ አድናቂ እና አወዳሽ ማግኘታቸውን የኢንዲፔንደንት መረጃ አመላክቷል፡፡ ስዊዘርላንዳዊው የማንቸስተር ሲቲው የተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች ማኑኤል አካንጂ ከእግር ኳስ ሙያው በተጨማሪ ታዋቂ የሒሳብ ባለሙያም ነው፡፡

የሊቨርፑል እና የብራዚል የግብ በር ጠባቂው አሊሰን ቤከር ጊታር ሲጫወት እና ሲዘፍን ምርጥ የሚባል ሙዚቀኛ እንደኾነ ይነገርለታል፡፡ የቀድሞው የአርሰናል እና የቼክ ሪፐብሊክ የአማካይ ተጨዋቹ ቶማስ ሮዚኪም በጊታሪስትነቱ ብዙ አድናቆት የተቸረው እግር ኳሰኛ ነው፡፡ የቶተንሃሙ እና የክሮሺያው የአጥቂ አማካይ ተጨዋች ኢቫን ፐርሲች ሀገሩን በእግር ኳስና በሐይቅ ዳር (ቢች) የቦሊቮል ጨዋታ ወክሎ መጫወት ችሏል። ፐርሲች እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 ለክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን የቢች ዳር የቦሊቮል ጨዋታ አድርጓል፡፡

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በሰውነታቸው ላይ ንቅሳት (ታቶ) ያሠራሉ፡፡ የቀድሞው የሊቨርፑል የተከላካይ መሥመር ተጨዋች ዳንኤል አገር ደግሞ የዘመናዊ ንቅሳት ወይም ታቶ ባለሙያ ነው፡፡ ዳንኤል አገር ከኳሱ ባሻገር ለሙያ አጋሮቹ በሰውነታቸው ላይ የሚፈልጉትን ዓይነት ታቶ የመሥራት ጥበብን የታደለም ነው፡፡

በቼልሲ እና በአርሰናል መለያዎች የምናውቀው ብራዚላዊው የተከላካይ መሥመር ተጨዋች ዴቪድ ሉዊዝም ከእግር ኳስ ሙያው በተጨማሪ የአስማት ጥበብ (ማጂሺያን) እንደኾነ ይነገርለታል፡፡ ሉዊዝ በቼልሲዎች ቤት እያለ ለጓደኞቹና ለአሠልጣኞች ያለውን የአስማት ጥበብ በማሳየት ያስደንቃቸው እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የቀድሞው የአርሰናል እና የሩሲያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂው አንድሬ አርሻቪንም ከእግር ኳሱ በተጨማሪ ተጓዳኝ መክሊት ከታደሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አርሻቪን የተዋጣለት የፋሽን ዲዛይነር መኾኑ በብዙ ሩሲያውያን ዘንድ ይታወቅለታል፡፡ በዚህም በሩሲያ አርሻቪን ከኳሱ ባልተናነሰ በፍሽን ሥራው ይቴወቃል።

በአርሰናል፣ በማንቸስተር ዩናይትድ፣ በኢንተር ሚላን እና በሌሎችም ክለቦች የተጫወተው ቺሊያዊው አሌክሲስ ሳንቼዝም ፒያኖ የሚባለውን የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ከእግር ኳስ ባሻገር ያለውን ተሰጥኦ ለብዙዎች አሳይቷል፡፡ የቀድሞው የቼልሲ እና የአርሰናል የግብ ጠባቂው የቼክ ሪፐብሊኩ ፒተር ቼክም የእጅ ጓንቶቹን አውልቆ ከበሮ (ድራም) ሲጫወትባቸው አጃኢብ እንደሚያሰኝ የብዙዎችን ምስክርነት አግኝቷል፡፡

የዓለማችን የእግር ኳሱ ምርጥ ባለ ተሰጥኦና የጽናት ተምሳሌቱ ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶም ጣፋጭ ምግቦችን ለራሱ በማዘጋጀት ምርጥ ሼፍ እንደኾነ ይነገርለታል። ስፔናዊው የቀድሞ የባርሴሎና ተከላካይ ጄራርድ ፒኬ ከእግር ኳሱ በተጨማሪ ምርጥ የቼዝ ተጨዋች ነው፡፡ ጀርመናዊው ተከላካይ ማትስ ሀልመስ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ፎቶ በማንሳት ራሱን ወደ ምርጥ ፎቶ አንሺነት የቀየረ ኾኗል፡፡

በቶተንሃም፣ በሪያል ማድሪድና በዌልስ ብሔራዊ ቡድን የምናውቀው ጋሬት ቤልም ከእግር ኳሱ በተጨማሪ በጎልፍ ጨዋታም ድንቅ ክህሎት እንዳለው አሳይቷል፡፡ ከላይ ያሉትን እግር ኳሰኞች ለአብነት ያህል አነሳናቸው እንጂ ብዙዎቹ ለአደባባይ ያልበቃ ብዙ መክሊትና ክህሎት እንዳላቸው እርግጠኛ መኾን ይቻላል፡፡

ብራዚላውያን የእግር ኳስ ተጨዋቾች በየሜዳው ከሚያሳዩን የሳንባ ዳንስ በተጨማሪ በርካታ አፍሪካዊያን ተጨዋቾችም የሀገራቸውን ውዝዋዜ ሲያስኮመኩሙን በቴሌቪዥን መስኮቶች ተመልክተናል፡፡ በእግር ኳሱ ሰማይ ሥር የእግሮቻቸውን ጥንካሬ ብቻ ያሳዩን እግር ኳሰኞች እንደ ኤሪክ ካንቶና በፊልም ተዋናይነት፣ እንደ ክላራን ሲዶርፍ በአቀንቃኝነት እና በሌሎችም ሙያዎች ውስጥ ውጤታማ ኾነው ዓይተናል፡፡

ወደፊትም ከሌሎች ክህሎቶቻቸው ጋር የምንተዋወቃቸው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ብዙ እንደሚኾኑ አያጠራጥርም፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here