ማንቸስተር ሲቲ ከቶትትንሃም የሳምንቱ የፕሪምየር ሊጉ ታላቅ ጨዋታ።

0
289

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክኒያት ተቋርጠው ሰንብተዋል። ነገር ግን ሊጎቹ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ይመለሳል።

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ነገ በ12ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይመለሳል። በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ማንቸስተር ሲቲ ከቶትንሃም የሚገናኙበት ጨዋታ ይበልጥ ተኩረት አግኝቷል።

የጋርዲዮላው ቡድን ከሚታወቅበት ሚዛን ወርዶ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን አስተናግዷል። ቡድኑ በሁሉም ቡድኖች አራት ተከታታይ ሽንፈት ገጥሞታል። የተጫዋቾች ጉዳት እና የፔፕ ጋርዲዮላ ቆይታ አጠራጣሪ መኾን ተጨምረው ለሲቲ ደጋፊዎች ነገሮች ተደበላልቀው ሰንብተዋል።

ነገር ግን በሜዳቸው ቶትንሃምን ከማስተናገዳቸው በፊት የደጋፊዎችን ቀልብ የሚሰበስቡ ዜናዎች ተሰምተዋል።

ጉዳት ላይ ከነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል ኬቨን ዲብሮይን፣ ካይል ዎከር፣ ማኑኤል አካንጅን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ተመልሰዋል።

ከምንም በላይ ደግሞ በዘጠኝ ዓመታት 18 ዋንጫዎችን ለክለቡ ያስገኘው አሠልጣኙ ጋርዲዮላ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በኢትሃድ ለመቆየት መስማማቱ በደጋፊዎች ዘንድ እፎይታን ፈጥሯል።

ሲቲ ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል በአምስት ነጥቦች አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ቶትንሃም ደግሞ ወጥ ባልኾነ አቋም ነው እስካኹን የመጣው። በሲቲ በሰባት ነጥቦች ተበልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጨዋታው ምሽት 2:30 የሚጀመር ይኾናል።

በሌሎች የቅዳሜ ጨዋታዎች ቀን 9:30 ሌስተር ከቼልሲ ይጫወታል። የቼልሲው አሠልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ የቀድሞ ክለባቸውን የሚገጥሙበት ይህ ጨዋታ ተኩረት አግኝቷል።

በተመሳሳይ 12:00 ላይ ደግሞ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። አርሰናል ከቶትንሃም፣ አስቶን ቪላ ከክሪስቲያል ፓላስ፣ ኤቨርተን ከብሬንት ፎርድ፣ በርንማው ከብራይተን እና ፍልሃም ከዎልቭስ ይጫወታሉ።

ቀሪ የ12ተኛ ሳምንት መርሐ ግብሮች እሑድ እና ሰኞ ይደረጋሉ። ሳውዝ አፕተን ከሊቨርፑል እሑድ 10 ሰዓት ይደረጋል።

ሊቨርፑል በ28 ነጥብ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን እየመራ ነው። ሳውዝ አፕተን ደግሞ በአራት ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጣል።

በተመሳሳይ ቀን 1:30 በአዲስ አሠልጣኝ የሚቀርበው ማንቸስተር ዩናይትድ ከኢፒስዊች ጋር ይጫወታል። ሮቨን አሞሪም የመጀመሪያ ሥራቸውን በዩናይትድ ቤት በሚጀምሩበት በዚህ ጨዋታ ቡድናቸው የሚያሳየው እንቅስቃሴ እና የሚያስመዘጎበው ውጤት ተጠባቂ ነው።

በጊዚያዊ አሠልጣኝ ቫኒስተሮይ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ዩናይትድ ኮቢ ማይኑን እና ሊኒ ዩሮን የመሳሰሉ ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾችን ግልጋሎት ሊያገኝ እንደሚችል ቢቢሲ በስፖርት ገጹ አስነብበቧል።

ዩናይትድ በ15 ነጥብ 13ተኛ ደረጃ ላይ ነው። ኢፒስዊች ደግሞ በስምንት ነጥብ 17ተኛ ደረጃ ላይ ተገኝቶ ነው በሜዳው የአሞሪምን ቡድን የሚያስተናግደው።

ኒውካስትል እና ዌስትሃም የሚገናኙበት ጨዋታ ደግሞ ሰኞ እንዲካሄድ መርሐ ግብር ተይዞለታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here