ለ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ተለይተዋል።

0
364

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ለመሳተፍ ሀገራት በምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎችም ተጠናቀዋል።

በዚህ መሠረት አዘጋጇ ሞሮኮን ጨምሮ ለ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የበቁ ሀገራት ተለይተዋል።

ከበፊቱ ደካማ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ የሚታይበት የምሥራቁ የአፍሪካ ክፍል በ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ሦስት ተወካዮችን አግኝቷል። ኡጋንዳ፣ ሱዳን እና ታንዛኒያ ከምሥራቅ አፍሪካ ለሞሮኮው ድግስ የበቁ ሀገራት ናቸው።

በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰው ሱዳን ለዚህ ክብር መብቃቷ ሙገሳን አስገኝቶላታል። ብሔራዊ ቡድኗ በግጭቱ ምክኒያት ጨዋታዎችን በሜዳው ማካሄድ አልቻለም። ነገር ግን ይሄ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ አላገደውም።

ከኢትዮጽያ ጋር በተመሳሳይ ምድብ የነበረችው ታንዛኒያ ሌላኛዋ በማጣሪያው ያልተጠበቀ ውጤት ያስመዘገበች ሀገር ናት።

በተለይ ትናንት ከጊኒ ጋር የነበረባትን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ነበረባት። በጨዋታው ብትሸነፍ ወይም ነጥብ ብትጋራ ኖሮ ወደ ሞሮኮ የመጓዝ ተስፋዋ ያከትም ነበር። ነገር ግን ጠንካራዋ ጊኒን በማሸነፍ ተሳትፎዋ አረጋግጣለች።

ከምድብ 1 ኮሞሮስ እና ቱኒዚያ፣ ምድብ 2 ላይ ሞሮኮ እና ጋቦን፣ ምድብ 3 ግብጽ እና ቦትስዋና፣ ናይጀሪያ እና ቤኒን ደግሞ ከምድብ አራት 2025ቱ የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ሀገራት ናቸው።

ምድብ አምስት ላይ አልጀሪያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ተያይዘው አልፈዋል፤ ጋናን የምድቡ ግርጌ ላይ ባስቀመጠው ምድብ 6 አንጎላ እና ሱዳን የሞሮኮ ጉዟቸውን አረጋግጠዋል።

ምድብ 7 ዛምቢያ እና ኮትዲቫር፣ ከምድብ 8 ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ታንዛኒያ ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል።

ከምድብ 9 ማሊ እና ሞዛምቢክ፣ ከምድብ 10 ካሜሮን እና ዝምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ ከምድብ 11 እንዲኹም ሴኔጋል እና ቦርኪናፋሶ ከመጨረሻው ምድብ ያለፉ ሀገራት ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here