ኳሱንም፣ ትምህርቱንም

0
258

ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አብዛኛዎቹ በትምህርታቸው ብዙም የገፉ እንዳይደሉ ይነገራል። ለዚህ በምክንያት የሚቀርበው ደግሞ እግር ኳሱ ላይ ማተኮራቸው የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ስለሚታሰብ ነው። ነገር ግን በእግር ኳስ ችሎታቸው አንቱ የተሰኙ ተጫዋቾች በትምህርቱም ዲግሪ የጫኑ እና ምሳሌ የሚኾኑ ብዙ ናቸው።

ለአብነትም የቀድሞውን የሊቨርፑል ተጫዋች ዱንካን ዋትሞር፣ ጃፓናዊው ዮቶ ናጋቶሞ፣ ስፔናዊው ሁዋን ማታ፣ ቤልጅየማዊው ሮሜሎ ሉካኩ፣ ኔዘርላንዳዊው ሩድ ቫኒስትሮይ፣ የኤስሚላኑ ተጫዋች ፊካዮ ቶሞሪ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የጣሊያኑ የመሐል ተከላካይ ጆርጂዮ ቼሌኒ በጣሊያን ብሔራዊ ቡድን እና በክለቡ ጁቬንቱስ ጠንካራ የመከላከል አቅሙን ያሳየ ተጫዋች ነው፡፡

በእግር ኳሱ ዓለም ከጣሊያን ብሔራዊ ቡድን እና ከክለቡ ጁቬንቱስ ጋር በስኬት የተረማመደው ቼሌኒ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ባለቤትም ጭምር ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ከቱሪን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በንግድ እና ምጣኔ ሃብት ያገኘው ቼሌኒ በዚያው ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን በማግኘትም ምሁሩ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመባል ችሏል፡፡

በማንቸስተር ሲቲ መለያ የአራት ፕሪምየር ሊጎች ድል ባለቤት የኾነው ቪሰንት ካምፓኒ ከአሊያንስ ማንቸስተር ቢዝነስ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የማስትሬት ዲግሪውን ያገኘ ሲኾን ሦሥተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪውን ደግሞ ከማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት በቅርቡ ይይዛል።

የነገው ዕጩ ዶክተር ቪሰንት ካምፓኒ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ከነበረው ስኬት ባሻገር በአሠልጣኝነት ሕይዎቱም የማንቸስተር ሲቲን ሁለተኛ ቡድን፣ በርንሌይን አሠልጥኗል። አሁን ላይ ደግሞ የጀርመኑን ባየር ሙኒክ በማሠልጠን ውጤታማነቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የአማካይ ተጫዋቹ ፍራንክ ላምፓርድም ከእግር ኳሳዊ ስኬቱ በተጨማሪ በትምህርቱም ዘርፍ የተሳካለት ተጫዋች ነው፡፡

ላምፓርድ ከቼልሲዎች ጋር ሦሥት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን ከፍ ያደረገ ሲኾን ገና የ17 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት ደግሞ ከብሬንትውድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል፡፡ ስፔናዊው የመሐል ሜዳ የኳስ ጥበበኛ አንድሬስ ኢኔስታ በእግር ኳሱ ዓለም ብዙ ታዳጊዎች አርዓያቸው የሚያደርጉት ተጫዋች ነው፡፡

የላማሲያ አካዳሚ ፍሬ የኾነው ኢኔስታ በእግር ኳስ ከተቸረው ክህሎት በተጨማሪ በባዮሎጂ እና ስፖርት ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ሁለት ዲግሪዎችን አግኝቷል፡፡ የቀድሞው የሊቨርፑል እና የቤልጅየም ግብ ጠባቂው ሲሞን ሚኖሌትም የተማሩ ከሚባሉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ከሉቨን ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ እና ሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘው ሚኖሌት የተማረው ትምህርት ከእንግሊዘኛ ቋንቋ በተጨማሪ የፈረንሳይ፣ ደች እና ጀርመንኛ ቋንቋዎችን በብቃት መናገር እንዳስቻለውም ተዘግቧል፡፡ እንደ ማርከስ ራሽፎርድ ያሉ ወጣትም የእግር ኳስ ተጫዋቾችም ከኳስ ብቃታቸው ባሻገር ለአዕምሯቸው ዕድገት ትምህርትን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው እየገፉበት ነው።

ዘ ኢንዲፔንደት በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራንን ዋቢ በማድረግ የተማሩ እግር ኳሰኞች ካልተማሩት በተሻለ በሜዳ ውስጥ ንቁ እና ቀልጣፋ መኾናቸውን ያስረዳል። ሌላው የጥናቱ አንድ አካል የኾነው ደግሞ ከእግር ኳስ በተጨማሪ የአካዳሚ ዕውቀት ያላቸው ተጫዋቾች እግር ኳስን በጉዳት ወይም በሌላ ምክንያት ቢያቆሙ በሠለጠኑበት ሙያ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን የማሥተዳደር አጋጣሚ እንደሚፈጠርላቸው ተጠቅሷል።

ለእግር ኳስ ተጫዋቾች የመማራቸው ጥቅም ተብሎ በሦሥተኛነት የተቀመጠው ደግሞ ከተጫዋችነት ወደ አሠልጣኝነት ሲሸጋገሩ ትምህርታቸው ለተሻለ ስኬት ያበቃቸዋል የሚለው ነው፡፡ በእግር ኳሱ የሚገኘውን ዝና እና ገንዘብ በአግባቡ ለመያዝም አዕምሮን ማስፋቱም ይመከራል።

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here