ባሕር ዳር: ኅዳር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 ታላቁ ሩጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አሥተዳደር ቢሮ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታወቁ፡፡ በየዓመቱ በአዲስ አበባ ከሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የኾነው ታላቁ ሩጫ ለ24ኛ ጊዜ ኅዳር 8 ቀን 2017 ይካሄዳል፡፡
በታላቁ ሩጫ 50 ሺህ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ውድድሩ መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ውድድሩ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ከመገንባቱ ባለፈ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመኾኑ ዓላማው እንዲሳካ መላው የመዲናዋ ነዋሪ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክት ተላልፏል።
ኅብረተሰቡ እስካኹን በከተማዋ በድምቀት የተከበሩ በዓላት እና የተከናወኑ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ትብብር እንዳደረገው ሁሉ ይህ ታላቅ ስፖርታዊ ውድድርም በሰላም እንዲካሄድ ከፀጥታ እና ደኅንነት አካላት ጎን በመኾን የፀጥታ ስጋት የኾኑ አጠራጣሪ ኹኔታዎችን ሲመለከት የፀጥታ እና ደኅንነት አካላት ጥቆማ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያበለፀገውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን(EFPApp) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ እና ደኅንነት አካላት በአካል በማድረስ የድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!