በእስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው የክለብ ፕሬዚዳንት

0
161

ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ድርጊቱ የተፈጸመው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2023 ተርክዬ ውስጥ ነው።

በተርክዬ ሱፐር ሊግ 20 ቡድኖች ይሳተፋሉ። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በታህሳስ 2023 የሪዚስፑር እና የአንካራጉኩ ቡድኖች የመርሐ ግብር የማሟያ ጨዋታቸውን አድርገዋል። ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉትን ጨዋታ አንድ አቻ በኾነ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታዎሳል።

በወቅቱም የአንካራጉኩ ቡድን ፕሬዚዳንት የነበረው ፋሩክ ኮካ የዕለቱ ዳኛ “ፍርደ ገምደል ውሳኔ ሰጥተዋል” በሚል የጨዋታው መቋጫ የፊሽካ ድምጽ እንደ ተሰማ ወደ ሜዳ በመግባት ዋና ዳኛ ሐሊል ዑሙት ሜለርን ዐይናቸውን በቡጢ በመምታት መሬት ላይ ዘርሯቸዋል።

የተርክዬ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወዲያውኑ ድርጊቱን በመቃወም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የእግር ኳስ ጨዋታ ለአንድ ሳምንት ያህል በማቋረጥ በኮካ ላይ የቋሚ ዕገድ ማስተላለፉን ቢቢሲ አስታውሷል።

ከዚህ በላይ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሷል። በተርክዬ መዲና አንካራ ውስጥ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተለው የነበረው ፍርድ ቤት ከሰሞኑ በዋለው ችሎት የ60 ዓመቱን ፋሩክ ኮካን በሦስት ዓመት ከሰባት ወር እስራት እንዳቀጡ መወሰን ቢቢሲ በስፖርት ገጹ ጽፏል።

ከፕሬዚዳንቱ እስር በተጨማሪ የአንካራጉኩ ቡድንም ሁለት ሚሊዮን ሊራ ወይም 54 ሺህ ፓውንድ እንዲከፍልም ተወስኖበታል።

በጥቃቱ የተሳተፉ ሌሎች ሦስት ተከሳሾችም ከ15 ወር እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

የአንካራጉኩ ክለብ በድረ ገጹ እንዳስነበበው ፋሩክ ኮካ ክለቡን በፕሬዝዳንትነት እየሠራ በቆየባቸው ሦስት ዓመታት ያበረከተው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር ብሏል።

ግለሰቡም በድርጊቱ ተጸጽቶ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here