ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ)አብዛኞቹ የእግር ኳስ ተጨዋቾች አሁን በሃብት ማማ ላይ ከመቀመጣቸው በፊት መነሻቸው ምንም የሚባል ነበር፡፡ ድህነት የቤተሰባቸው አንዱ አካል እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ ላይ በጥረታቸው ከድህነታቸው ጋር ተለያይተዋል፡፡
እግር ኳስ ብዙ ዝነኞችን ከድህነታቸው አላቅቆ ለእውቅና እና ለሃብት አብቅቷቸዋል፡፡ መነሻቸው ከድሃ ቤተሰብ የነበሩ አንዳንድ ተጨዋቾች ኳስ በእግራቸው ሥር ስትገባ ድህነታቸውን በእግራቸው ስር ያገኙት ያህል እያንከባለሉ እንደ ቆሻሻ መረብ ውስጥ ጥለውታል፡፡
አሌክሲስ ሳንቼዝ፣ አንሄል ዲማሪያ፣ ዳኒ አልቬስ፣ ሉካ ሞድሪች እና ኔይማር ጁኒየር አሁን የደረሱበት ቦታ ከመድረሳቸው በፊት ከቤተሰባቸው ጋር ኾነው በድህነት አለንጋ ተገርፈዋል፡፡ እንደማንኛውም የሀገራቸው ድሃ ማኅበረሰብ በችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ ዛሬ ግን ያንን ችግራቸውን በጥረታቸው ድል ነስተው ዝነኛም ሃብታምም ኾነዋል፡፡
ቀጣዮቹ አምስት ተጨዋቾችም ከምንም ተነስተው ዝነኛ እና ሃብታም የኾኑ ተጨዋቾች ናቸው። የኡራጋዩ ሉዊስ ሱዋሬዝ በልጅነቱ ከእኩዮቹ ጋር በባዶ እግሩ ኳስ የሚጫወት ድሃ እና የድሃ ልጅ ነበረ። ወላጆቹ እሱ ገና የ9 ዓመት ለጋ ዕድሜ ላይ እያለ በመለያየታቸው ምክንያት ሱዋሬዝ በጣም ክፉ እና ነጭናጫ ባህሪ ያለው ልጅ ኾኖ አድጓል፡፡
ሱዋሬዝ አብዝቶ የደከመለት እግር ኳስ ውለታውን ከፍላው አሁን በሃብት ማማ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሱዋሬዝ አያክስ፣ ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ኢንተር ሚያሚ የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው፡፡
ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ባምባሊ በምትባል ትንሽዬ መንደር ውስጥ ነው የተወለደው። የማኔ አባት ልጃቸው እግር ኳስን እንዳይጫወትና ይልቁንም በሃይማኖቱ እንዲጠነክር ያበረታቱት ነበር። ማኔ ግን ገና በልጅነቱ እግር ኳስ የሕይዎት ጥሪው እንደኾነ አውቆ ከሠፈር ጓደኞቹ ጋር እግር ኳስ መጫወትን ቀጥሏል፡፡
በአንድ ፈረንሳዊ ስካውት በኩል የእግር ኳስ ክህሎቱ የታወቀለት ማኔ በእግር ኳስ ከድህነት ሕይዎቱ መውጣት ችሏል፡፡ በእግር ኳስ ብዙ ዝና እና ሃብት ቢያገኝም ያደገበትን ማኅበረሰብ ባለመዘንጋት እንደ ውድ ስልክ፣ መኪና፣ ጌጧጌጦች እና ቅንጡ ከኾነ ኑሮ ርቆ ለሀገሩ ዜጎች ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት በመገንባት ስሙ ከድህነት ይልቅ ከደግነት ጋር ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
ማኔ ሬድቡል ሳልስበርግ፣ ሳውዝአምፕተን፣ ሊቨርፑል፣ ባየር ሙኒክ እና አልናስር የተጫወተባቸው ክለቦቹ ናቸው፡፡
ስዊድናዊው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ደንዳና ተክለ ሰውነቱን ለተመለከተው ከድህነት ጋር ፈጽሞ የማይተዋወቅ ሊመስለው ይችላል፡፡ አንድ ቀጫጫ እና ድሃ ስውዲናዊ ከዓመታት በኋላ በእግር ኳስ የሚፈራና ግዙፍ አጥቂ ይኾናል ብሎ ለመገመት ነብይነትን የጠይቃል፡፡
በስዊድኑ ማልሞ ክለብ ፕሮጀክት ውስጥ ኳስን የጀመረው ዝላታን ከብዙ ጥረት እና ልፋት በኋላ ዝነኛም ሃብታምም የእግር ኳስ ተጨዋች መኾን ችሏል፡፡
ኢብራሂሞቪች በማልሞ፣ አያክስ፣ ጁቬንቱስ፣ ኢንተር ሚላን፣ ባርሴሎና፣ ኤስ ሚላን፣ ፒኤስ ጂ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኤልኤ ጋላክሲ የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው፡፡
እንደ ፎርብስ መጽሔት መረጃ ከኾነ የዓለማችን ቁጥር አንድ የስፖርተኞች ሃብታም የኾነው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በድህነት ውስጥ ማቅቆ ለዝና እና ለሃብት የበቃ መኾኑን የምናውቅ ጥቂቶች ነን፡፡ አባቱ የአልኮል ሱሰኛ ስለነበሩ እናቱ አራት ልጆችን ለማሳደግ በጣም ተፈትነዋል፡፡ ዝነኛው የእግር ኳስ ሰው በእናቱ ከመጡበት በምንም ነገር ላይ የማይደራደረውም የእናቱ ውለታ የበዛ ስለመኾኑ የጎል ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል፡፡
ብዙ ጥሩ ህልሞች የነበሩት ታዳጊው ሮናልዶ ከትንሽዬዋ የማዴራ መንደር ተነስቶ በትላልቅ ስታዲየሞች ውስጥ ታሪክ የማይረሳቸውን ገድሎች በእግሮቹ ጽፏል፡፡ “CR 7” በሚባሉት የንግድ ተቋማቱ የሚታወቀው ሮናልዶ እስከ 2023 ድረስ 690 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የተጣራ ሃብት እንዳለውም ተዘግቧል፡፡
ሮናልዶ በስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ፣ ጁቬንቱስ እና አልናስር ክለቦች ተጫውቷል፡፡
በታሪክ ታላቁ የእግር ኳስ ተጨዋች እየተባለ የሚጠራው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ታላቅ ከመኾኑ በፊት በልጅነቱ የድህነት ሕይወትን ዓይቶ አልፏል፡፡ የፋብሪካ ሠራተኛ የነበሩት አባቱ ብዙም ገቢ ስለማያገኙ ማራዶና እና ቤተሰቦቹ የድህነትን ሕይዎት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡
አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ በብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ እስከ መመለክ የደረሰ ሰው ነው፡፡ የሕይዎት ጅማሬው ግን ከስኬት ጋር ሳይኾን ከድህነት ጋር የተቀራረበ ነበር፡፡
ማራዶና ቦካ ጁኒየርስ፣ ባርሴሎና እና ናፖሊ በጣም የገነነባቸው ክለቦቹ ናቸው፡፡
ዘጋቢ፦እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!