የሀንሲ ፍሊክ አብዮት!

0
175

ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባርሴሎና በስፔንም ይሁን በአውሮፓ ጠንካራ ከሚባሉ ግንባር ቀደም ክለቦች ውስጥ አንዱ ነው። ክለቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቀድሞው የክለቡ ድንቅ ተጫዋች ዣቪ አሠልጣኝነት ሲመራ ነበር። ዣቪ በመጀመሪያ ዓመቱ ክለቡ የላሊጋ ዋንጫ እንዲያነሳ አድርጓል። ነገር ግን ክለቡ የሚታወቅበትን የአጨዋወት ስልት በማስቀጠል እና ወጥነት የጎደለው እንቅስቃሴ በተጫዋችነት በነገሰበት ኑ ካፕ በአሠልጣኝነት መድገም ሳይችል እንዲሰናበት ምክንያት ኾኗል።

ባርሴሎና ዣቪን አሰናብቶ ጀርመናዊ ሀንሲ ፍሊክን በመቅጠር ነው የዘንድሮውን የውድድር ዘመን የጀመረው። ክለቡ በገንዘብ ችግር ምክንያት ተጫዋቾችን ማስፈረም ባይችልም በላማሲያ አካዳሚ ውጤት የተጫዋቾች የእስካሁን ጉዞው የሰመረ ኾኗል። ሀንሲ ፍሊክም ክለቡ ላይ የፈጠሩት አብዮት በብዙ እያሥመሠገናቸው ነው።

ቡድኑ በላሊጋው 12 ጨዋታዎችን አድርጎ 11ዱን አሸንፏል። በአንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት አስተናግዷል። 33 ነጥቦችን በመሠብሠብ ከምንጊዜም ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ በዘጠኝ ነጥብ በልጦ ሊጉን እየመራ ነው። ባርሴሎና በሻምፒዮንስ ሊጉም መንገዱ የተሻለ ነው። ከአደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሦሥቱን በማሸነፍ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በታዳጊዎች የተዋቀረው የሀንሲ ፍሊኩ ቡድን በማጥቃቱ እጅግ አስፈሪ ኾኖ ቀርቧል። የሉዋንዶስኪ፣ ያማል እና ራፊኛ ጥምረት ታላላቅ በሚባሉ ቡድኖች ላይ ሳይቀር ምረት የለሽ ኾኖ ታይቷል። ባየር ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ ደግሞ ለዚህ ምሳሌ ናቸው። ባየር ሙኒክ በሻምፒዮንስ ሊጉ፣ ሪያል ማድሪድ ደግሞ በላሊጋው የአራት ጎል ናዳን የቀመሱ ክለቦች ናቸው።

ያሆ ስፖርት የዘንድሮው የባርሴሎና ቡድን በላሊጋው በአማካኝ ዕድሜ ትንሹ ቡድን መኾኑን ይገልጻል። የክለቡ አመካኝ ዕድሜ ደግሞ 24 መኾኑን ያስረዳል። የላማሲያ ፍሬዎቹ ጋቪ፣ ፔድሪ፣ ያማል እና ባልዴ ቀደም ብለው የክለቡ ሁነኛ ተጫዋች ኾነዋል። ዘንድሮ ደግሞ ሎፔዝ እና ኩባርሲን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ከዕድሜያቸው በላይ ክለቡን እያገለገሉ ነው።

ባርሴሎና አኹን ላለበት የተሳካ መንገድ ከአካዳሚው ላማሲያ በተጨማሪ ለጀርመናዊ አሠልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ ምሥጋና እየጎረፈላቸው ነው። አሠልጣኙ ባርሴሎናን እየመሩ እስካሁን 15 ጨዋታዎችን አድርገዋል። 13 ቱን ሲረቱ ሁለቱን ተሸንፈዋል። 86 ነጥብ 6 በመቶ ጨዋታዎችን ያሸንፉሉ፣ በጨዋታ በአማካኝ 3 ነጥብ 3 ግብ ቡድናቸው ተጋጣሚዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 0 ነጥብ 93 ግቦች ደግሞ ይቆጠሩበታል።

እነዚህ ቁጥሮች ከጋርዲዮላው የ2008/2009 የባርሴሎና ቡድን የአሁኑ እንደሚሻል ያሳያሉ። ያኔ በዓመቱ መጨረሻ የሻምፒዮንስ ሊጉ፣ የላሊጋ እና የኮፖ ዴላሬይ ዋንጫን ያነሳው የጋርዲዮላው ሥብሥብ በመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎች የነበረው ስኬታማነት ከአሁኑ የፍሊክ ቡድን ያነሰ ነው። ለአብነት ከ15 ጨዋታዎች ያሸነፈው 11ዱን ነበር። በሁለቱ አቻ ወጥቶ፣ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፎ ነበር። 73 ነጥብ 3 በመቶ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ፣ 13 በመቶ ደግሞ ተሸንፏል።

ይህም በዓመቱ መጨረሻ ክለቡ የሚያስመዘግበው ውጤት ለወደፊት የሚታይ ኾኖ በመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች ሚዛን ግን ሀንሲ ፍሊክ ከጋርዲዮላ የተሻሉ መኾናቸውን ያሳያል። ፕላኔት ፉትቦል የተሰኘ የመረጃ ምንጭ የያኔው ባርሴሎና መሲ፣ ኢኔስታ፣ ዣቪ እና ፒዮልን ጨምሮ በርካታ ኮከቦችን የያዘ እንደነበር አስታውሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here