ታይቶ የጠፋው ኮከብ!

0
313

ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2000 መጀመሪያ ላይ ብራዚላዊውን ሮናልዶ ናዛሪዮ ዴሌማን በመተካት የብራዚል ቀጣዩ ፊት አውራሪ ይኾናል ተብሎ የተጠበቀው አድሪያኖ መጨረሻው እንደተጠበቀው አልኾነም፡፡ ግዙፉ አጥቂ በተለይ ጨዋታ በጀመረበት የብራዚሉ ፍላሚንጎ ክለብ እና በጣሊያኑ ኢንተርሚላን ያሳየው ብቃት የእግር ኳስ ሀገሯ ብራዚል ቀጣይ ተስፋዋ እንዲኾን አድርጎት ነበር፡፡

የአድሪያኖ በእግር ኳስ የደመቀ ታሪክ ከብርሃን ወደ ጨለማ የተቀየረው በቅጽበት ነው፡፡ እሱም ከአባቱ ሞት በኋላ በዘጠኝ ቀናት ውስጥ ሕይዎቱን ከገነት ወደ ሲኦል እንዴት እንዳሸጋገረው ከትሪቡን ጋር አድርጎት በነበረው ቃለ ምልልስ አሳውቋል፡፡ ግዙፍ ተክለ ሰውነቱ የብዙ ተከላካዮች ራስ ምታት የነበረው ብራዚላዊው ተስፈኛ በጣሊያን እና በሪዮ ዴጄኔሮ ጎዳናዎች ላይ ሠክሮ ሲንገዳገድ ማየትን ማንም ሰው አልጠበቀውም፡፡ ከአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ጋር ይገናኛል ብሎ ለማሰብም ይቸግር ነበር።

የአድሪያኖ አስደናቂ ግቦች፣ አስደናቂ ስኬቶች እና አስደማሚ ታሪኮቹ በቅጽበት ወደ አሳዛኝ ታሪክነት የተቀየሩት እ.ኤ.አ በ2016 ነው፡፡ አድሪያኖ በ2016 ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ሲለያይ እንደ ሌሎች የእግር ኳስ ተጫዋቾች ስንብት ተደርጎለት ሳይኾን በድንገተኛ ውሳኔ ነው፡፡ ይሄው ድንገተኛ የእግር ኳስ ማቆም ውሳኔውም በዋና ክለቡ እና በውሰት በወሰዱት ክለቦች ክስ እንዲመሠረትበት አድርጎት ወደ ፍርድ ቤቶች እንዲመላለስ አስገድዶታል፡፡

ከነበረው ከፍታ በአፍታ ወደ ዝቅታ የወረደው አድሪያኖ በእጁ ቢራ ይዞ በባዶ እግሩ ጎዳና ላይ ሲንገዳገድ የሚያሳይ ምስል ለዓለም ሕዝብ ከመሠራጨቱ ጋር ተያይዞ፣ ይህ ሰው የጤናው ጉዳይ እጅግ ወደሚያሳስብ ኹኔታ ደርሷል እንዲባል አስችሏል፡፡ እንደ ሜይል ኦን ላይን ዘገባ ከኾነ የ42 ዓመቱ አድሪያኖ በከፋ የአካል እና የአዕምሮ ጤንነት ችግር ውስጥ መኾኑን አመላክቷል፡፡

በሙሉ ስሙ ሌይት ሪቤሮ አድሪያኖ ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ የተወለደው በቪላ ከሩዜሮ ብራዚል ውስጥ ነው፡፡ ከሪዮ በላይ ባሉ ኮረብታዎች ውስጥ ከሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ ድሃ ብራዚላዊያን ወላጆቹ የተፈጠረው አድሪያኖ ምንም እንኳን የልጅነት ሕይዎቱ በድህነት የታጠረ ቢኾንም ደስተኛ እንደነበረ በ2021 ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጿል፡፡

ወርቃማ እግሮቹ የራሱን እና የቤተሰቦቹን ድህነት መጨፍለቅ ያስቻሉት የቀድሞው የብራዚል እና የኢንተር ሚላን ድንቅ አጥቂ፣ የብራዚሉን ፍላሚንጎ ክለብ አካዳሚ የተቀላቀለው ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ የስኬቱ መነሻም ይሄው የብራዚሉ ፍላሚንጎ ክለብ ነው፡፡ በ18 ዓመቱ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን መጠራት ያስቻለውን ብቃት ያሳየው አድሪያኖ በኢንተር ሚላን ድንቅ ጊዜን ከማሳለፉ በተጨማሪ ለፊዮሮንቲና እና ፓርማ ክለቦችም በውሰት በመጫወት አሳልፏል፡፡

የአድሪያኖ ሕይዎት ከብርሃን ወደ ጨለማ ያመራው የአባቱን ሞት ተከትሎ እንደኾነ ይገመታል። እሱም የሚገልጸው ይሄንኑ ነው፡፡ ከአባቱ ሞት በኋላ ወደ ጠጭነት ያመራው ግዙፉ አጥቂ በኢንተር ሚላን እየተጫወተ ባለበት ወቅት በሥካር ምክንያት ብዙ ቀናት ከልምምድ እና ከጨዋታ ሳይቀር ስለመቅረቱ ተዘግቧል፡፡

̎አባቴን ሳጣ በጣሊያን ውስጥ ብቻዬን የቀረሁ ያህል ተሰምቶኛል። ብቸኝነቴን ለመርሳት ስልም ሆዴ የቻለውን ያህል ወይን፣ ውስኪ፣ ቮድካ፣ ቢራ እና ሌሎችንም አልኮሎች ጠጥቻለሁ፤ በመጨረሻም ኢንተርን መልቀቅ ስለነበረብኝ ለቅቄያለሁ ብሏል፡፡ አድሪያኖ ከትሪቡን ጋር አድርጎት በነበረው ቃለ ምልልስ አደንዛዥ ዕጽ ፈጽሞ እንደማይጠቀም ተናግሯል፤ አብዝቶ እንደሚጠጣ ግን አልደበቀም፡፡ ̎እግዚአብሔር አባቴን በድንገት ሲነጥቀኝ እኔ እንደዚህ እንደምኾን ማወቅ ነበረበት”̎ ሲልም ለውድቀቱ ፈጣሪውን ተጠያቂ አድርጓል፡፡

በኛ ሀገር አንድ ሰው ከነበረው ጥሩ ደረጃ ወደ ዝቅታ ሲያመራ ̎ወጣ ወጣ እና እንደ ሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” ተብሎ ይተረትበታል፡፡ አድሪያኖም የኾነው እንዲሁ ነው፡፡ የብራዚል የአጥቂ መሥመር የረጅም ጊዜ ተስፈኛ የነበረው አድሪያኖ በሁሉም ነገሮቹ ለታዳጊ ብራዚላውያንም ኾነ ለሌሎች የዓለም ታዳጊ ተስፈኞች አርዓያ መኾን ሳይችል ቀርቷል፡፡

ግዙፉ አጥቂ አሁን ላይ በጎዳናዎች ላይ የቢራ ጠርሙስ ጨብጦ እየተንገዳገደ የሚታይ፣ ዝና እና ክብሩን ለሥካር አሳልፎ የሰጠ፣ ኳስ አክርረው የሚመቱለት እግሮቹ ሥካር የሚያወላክፋቸው ሰንበሌጦች ኾነውበታል፡፡ አድሪያኖ “የውድቀቴ መንስኤ የአባቴ ሞት ነው” ይበል እንጂ የውድቀቱ መንስኤ ተሰጥኦውን አለማክበሩ እና ዝናውን መቋቋም አለመቻሉ ነው፡፡ በርካታ ብራዚላዊያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች እንደ አድሪያኖ ኹሉ ከድሃ ቤተሰብ እና ከትንሽ መንደር ውስጥ ወጥተው ወደ ከፍታ ሲያመሩ የከፍታ ኑሮን በአግባቡ መምራት ባለመቻል ቁልቁል ወርደዋል፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here