ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ወሳኝ ከኾኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ታማኝነት ነው፡፡ ጋዜጠኞች ታማኝ መኾን ያለባቸው ለአድማጮቻቸው፣ ለተመልካቾቻቸው እና ለአንባቢዎቻቸው ብቻ ሳይኾን ለሙያቸውም ጭምር ነው፡፡ ዓለም ላይ ለሙያቸው ታማኝ የኾኑ እና ለሙያቸው የበዛ መስዋዕትነት የሚከፍሉ በርካታ ሙያተኞች አሉ፤ ጣሊያናዊው የስፖርት ጋዜጠኛም ከእነዚሁ ሙያተኞች ውስጥ እንደ አንዱ ይፈረጃል፡፡
ጣሊያናዊው ፋብሪዚዮ ሮማኖ የተወለደው በ1993 (እ.ኤ.አ) በጣሊያኗ ኔፕልስ ከተማ ነው። በስፖርት ጋዜጠኝነቱ እና በታማኝ የዝውውር ዘገባዎቹ የሚታወቀው ፋብሪዚዮ ሮማኖ ሚላን ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ተምሯል። ሮማኖ የጋዜጠኝነት ሥራን የጀመረው በ18 ዓመቱ ነው። ያኔ የባርሴሎና ተጫዋቾችን በተመለከተ ብቻ በባርሴሎና ከሚገኝ ጣሊያናዊ ወኪሉ መረጃዎችን እየተቀበለ ይዘግብ ነበር::
በ19 ዓመቱ ስካይ ስፖርት ጣሊያንን ከተቀላቀለ ጀምሮ ግን በመላው አውሮፖ ከሚገኙ ክለቦች፣ ወኪሎች እና አሠልጣኞች ጋር ግንኙነት መፍጠር ችሏል። ለስካይ ስፖርት፣ ለዘጋርዲያን፣ ለሲቢኤስ እና ለኦፍሳይድ ዘጋቢ ኾኖም ሠርቷል፡፡ አሁን በጣም ታዋቂ ከኾኑ የእግር ኳስ ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ የኾነው ፋብሪዚዮ ሮማኖ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን መዘገቡን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን በማኅበራዊ ገፆች አፍርቷል።
በዝውውር ዘገባዎቹ አብዝቶ የሚታወቀው ፋብሪዚዮ ሮማኖ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት የስፖርት ጋዜጠኛ ነው። የፋብሪዚያኖ ተከታዮች ከአንዳንድ ስመ ጥር ክለቦችም የበዙ እንደኾኑ ይነገርለታል፡፡ እንግሊዘኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ፖርቹጋልኛ እና ስፖኒሽ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረው የስፖርቱ ታማኝ ጋዜጠኛ ሮማኖ የእንግሊዙ ዋትፎርድ ክለብ ደጋፊ ስለመኾኑም ይነገራል።
ከመጋረጃው ጀርባ ባሉ የእግር ኳስ ዝውውሮች “ነብይ” እየተባለ የሚወደሰው ፋብሪዚዮ ሮማኖ በተለይም በአውሮፖ ኀያላኑ ሊጎች ማለትም የእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ፣ የስፔኑ ላሊጋ፣ የጣሊያኑ ሴሪኤ፣ የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ እና የፈረንሳዩ ሊግ አንድ የተጫዋቾችን ዝውውር ሲገልጽ የሚቀድመው ሚዲያ የለም።
በአንድ ወቅት ፋብሪዚዮ ሮማኖ ጃፓናዊው የመሐል ተከላካይ ማያ ዮሺዳ ከእንግሊዙ ሳውዝአምፕተን ክለብ ወደ ጀርመኑ ሻልክ 04 በነጻ መዛወሩን ፈጥኖ መረጃ ያጋራል፡፡ ይህንን መረጃ ከራሱ በቀር ሚስቱ እንኳን እንደማታውቅ እርግጠኛ የነበረው ዮሺዳ ”ይህ ሰው በጣም አስገራሚ ነው፤ ለሚስቴ እንኳን ያልነገርኳትን ዝውውር እንዴት እንዳወቀው አስገርሞኛል፤ ለማንኛውም አድናቂው ነኝ” ሲል ግርምቱን በኤክስ ገጹ አጋርቷል፡፡
ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዮሺዳ ላጋራው አድናቆት ምላሽ ሲሰጥ ”ወንድም ዮሺዳ፣ ከዚህ በኋላ ሚስትህ የኔን ገጽ እንድትከታተል ንገራት፤ አንተ ወዴት ሀገር እና የት ክለብ እንደምትጫወት ከኔ ቀድሞ የሚያሳውቃት የለምና” ሲል ምላሽ ሰጥቶታል፡፡
ፋብሪዚዮ ሮማኖ “ታማኙ ጋዜጠኛ” የሚለውን ቅጽል ስም ያገኘው በሥራዎቹ ታማኝነት ነው። በእሱ ስም ማኅበራዊ ገፆች ላይ የሚለጠፉ ዝውውሮችም ኾኑ በእሱ አንደበት የሚነገሩ አጓጊ ዝውውሮች ዕውነተኛነታቸው መቶ ከመቶ መኾኑን የዓለም እግር ኳስ ወዳዶች ሁሉ ከተማመኑበት ሰነባብተዋል።
ፋብሪዚዮ ሮማኖ ያልተረጋገጡ እና ታማኝ ያልኾኑ የዝውውር ዘገባዎችን አይዘግብም። ለታማኝነቱ ቅድሚያ ይሰጣል የሚባለው ሮማኖ የጭምጭምታ ዘገባዎችን አጥርቶ በማሳወቅም ይታወቃል።
ለአብነት እከሌ የሚባለው ተጫዋች በእከሌ ክለብ ይፈለጋል የሚሉ ጭምጭምታዎች ቢበዙ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ስለዚህ ጉዳይ ወይም ዝውውር ምን ይላል? ተብሎ በጉጉት ይጠበቃል።
ፋብሪዚዮ ሮማኖ በጭምጭምታነት የሚነሱ ጉዳዮችን ከመሠረቱ በማጥራት የተባለው ተጫዋች በተባለው ቡድን መፈለጉን ወይም አለመፈለጉን በተጨባጭ ማስረጃ ለሚዲያዎች ያቀርባል። ያ ተጫዋች በዚያ ክለብ ስለመፈለጉ ወይም አለመፈለጉ ዕውነተኛ የሚኾነው መረጃ ሮማኖ ያለው ብቻ ነው፤ እንደ ስካይ ስፖርት ዘገባ።
የኛም ሀገር የስፖርት ጋዜጠኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዝውውር ጉዳዮችን ሲያነሱ “ታማኙ የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ እንዳረጋገጠው” ማለት ጀምረዋል።
ይህ ደግሞ የሚያሳየው የፋብሪዚዮ ሮማኖ ታማኝ የመረጃ ምንጭነት ወይም ታማኝ የስፖርት ጋዜጠኝነት ዓለም አቀፍ ዕውቅና እያስገኘለት መምጣቱን ነው።
በተደጋጋሚ ያገኛቸው የተለያዩ ሽልማቶችም ለዚህ ማሳያ ናቸው። ፍብሪዚዮ አሁን በሚያወጣቸው አውነተኛ የዝውውር ወሬዎች በመላው ዓለም ይታወቃል። ይህም በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጎታል።
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!