ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ በ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር)፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ፣ የካፍ የኢትዮጵያ ተወካይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትስፔ ወደ ኢትዮጵያ ለ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በቆይታቸውም የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንደሚመክሩም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ኮንጎ ብራዛቪል በገጠማት ወረርሽኝ ምክንያት ማስተናገድ ያልቻለችውን ጉባኤ ማዘጋጀቷ፣ ሀገሪቱ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት የምታደርገውን ጥረት አጉልቶ ያሳያልም ተብሏል።
ለዚህ ጉባኤ የአዲስ አበባ ምርጫ ከተማዋ በአፍሪካ ስፖርት ላይ ያላትን ተፅእኖ እና ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ ብቃቷን ያሳያል ።
የ46ኛው የካፍ ጉባኤ ከተለያዩ አባል ማኅበራት ተወካዮች መካከል የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ውይይቶች እና የአህጉሩን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል።
ጠቅላላ ጉባኤው የአፍሪካ እግር ኳስን የሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮችን ለአብነት የስፖርቱ የልማት ስትራቴጂዎች፣ የአሥተዳደር ጉዳዮች እና ቀጣይ አህጉራዊ ውድድሮች ቅድመ ዝግጅቶችን ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤው በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃን ከፍ ለማድረግ በሚደረገው የትብብር ጥረት ላይ አባል ማኅበራት እንዲወያዩበት እድል ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የካፍ ፕሬዚዳንት እና ሌሎች ቁልፍ ሰዎች መገኘታቸው እነዚህ ውይይቶች ስፖርቱን በአህጉሪቱ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለውን ጠቀሜታ አጉልቶ እንደሚያሳይም ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ የ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኾና መመረጧ ሀገሪቱ በአፍሪካ የእግር ኳስ እደገትን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ትልቅ ክስተት ነው።
ስብሰባው የአፍሪካን እግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የሚያጎለብቱ አዳዲስ ጅምሮች እና አጋርነቶች መንገዱን ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢቢሲ እንደዘገበው 46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ፕሮግራሞች ይካሄዳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!