ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ሰባት ጎል ተቆጥሮበት ሽንፈት በማስተናገድ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድሉን አመንምኖ መመለሱ ይታወሳል።
በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ አሠልጣኙ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያሳያል። ከተነሳላቸው ጥያቄዎች መካከል እንደ አንድ ግለሰብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እየተመዘገበ ባለው ውጤት በግልህ ኢትዮጵያ ስትሸነፍ ምን ይሰማሀል? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ
“ኢትዮጵያ ስትሸነፍ ከእናተ የተለየ ስሜት አይኖረኝም። ከአንተ በላይ ነው የምቆረቆረው። እኔ ተዋናይ ስለሆንኩ እናንተ ተዋንያን ላትሆኑ ትችላላችሁ እኔ ደግሞ ከማንም በላይ እጎዳለው ስሜቱ በጣም ከባድ ነው። የምንችለውን ያህል ነው ጥረት የምናደርገው። አኹን መታወቅ ያለበት ተጨባጭ አቅማችንን ማወቅ አለብን። አንዳንድ ጊዜ ስሜታዊ መኾን አያስፈልግም። ከጊኒ ጋ ተጨባጭ የአቅም ልዩነት አለን እንደ ቡድን ጠንካራ ሀገር ነው። በተቻለ መጠን ያለውን ልዩነት አጥብበን ተፎካክረን ለመውጣት ጥረት አድርገናል። ያም ቢሆን የፍጥነት ልዩነት ይጎላል። በተለይ የመከላከሉ ላይ እና ኳስ ስናጣ የምናደርገው እንቅስቃሴ የለም። የምንጫወተው ኳስ ስናገኝ ብቻ ነው። ይህ በጣም መታረም ያለበት ሥራ የሚፈልግ ነገር ነው።”
በቀጣይ ከብሔራዊ ቡድን ጋር የሚኖራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ሲናገሩ “ከአምስት ቀን በኋላ እለቃለሁ ውሉ በ23 ነው የሚያልቀው ምን እንደሚያስጨንቃችሁ አላውቅም። ውሉ ሲጠናቀቅ እለቃለሁ በማለት ተናግረዋል።”
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!