ስምንት ሀገራት ለ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

0
255

ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሞሮኮ 35ኛውን የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ የምታዘጋጅ ሀገር ናት። በ12 ምድብ ተከፍለው ሀገራት ለውድድሩ ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው። የየምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ትናንት ሲጠናቀቁ ስምንት ሀገራት የሞሮኮ ትኬታቸውን በእጃቸው አስገብተዋል።

ከምድብ ሁለት ሞሮኮ አራቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ችላለች። ነገር ግን ሞሮኮ አዘጋጅ በመኾኗ በቀጥታ የማለፍ እድልም ነበራት። በዚሁ ምድብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለችው እና ሰባት ነጥብ የሰበሰበችው ጋቦን የተሻለ የማለፍ እድል አላት። ማዕከላዊ አፍሪካ ደግሞ ሦስት ነጥብ ይዛ በቀሪ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች እድሏን ትሞክራለች።

ምድብ ሦስትን ግብጽ በበላይነት እየመራች ነው። 12 ነጥብ በመሰብሰብ ቀድማ ማለፏ እውን ኾኗል። ቦትስዋና በስድስት ነጥብ ስተከተል፣ ቀሪ የምድቡ ቡድኖችም የማለፍ እድል አላቸው። አልጀሪያ ከምድብ አምስት ለሞሮኮው ድግስ ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠች ሀገር ናት። ያደረገቻቸውን አራት ጨዋታዎችንም ማሸነፍ ችላለች። ከዚሁ ምድብ ኢኳቶሪያል ጊኒ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ኾኖ የማለፍ እድል እጇ ላይ ይገኛል።

ምድብ ስድስት ላይ ያልተጠበቀችው አንጎላ በቀላሉ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች። በ12 ነጥብ የምድቡ አናት ላይ የተገኘችው አንጎላን በመከተል በሰላም እጦት የምትታመሰው ሱዳን በሰባት ነጥብ እየተከተለች ነው። ጋና ከዚህ ምድብ በተጠበቀችበት ልክ ባለመገኘቷ ሁለት ነጥብ ብቻ በአራት ጨዋታ በመሰብሰብ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች።

ለኢትዮጵያ የከበደው ምድብ ስምንት ለዲሞክራቲክ ኮንጎ ቀላል ኾኗል። ኮንጎ አራቱን ጨዋታዎች አሸንፋ ሞሮኮ መገኘቷን አረጋግጣለች። ኢትዮጵያ ላይ በደረሶ መልስ ስድስት ነጥብ የወሰደችው ጊኒ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች እድሏን በራሷ ትወስናለች። ምድብ 10 ላይ ካሜሮን ቀድማ ያለፈች ሀገር ናት። ከአራት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፋ፣ በአንዱ ነጥብ የተጋራችው ካሜሮን በ10 ነጥብ ማለፏን አረጋግጣለች።

ስምንት ነጥብ የያዘችው ዚምባብዌ እና በአራት ነጥብ ሦስተኛ ላይ የምትገኘው ኬኒያ የማለፍ እድላቸው በቀጣይ ጨዋታዎች ይወሰናል። ምድብ 12 ብቸኛው የምድብ ሁለቱንም አላፊዎች የተለዩበት ነው። ቡርኪናፋሶ እና ሴኔጋል ከምድቡ እያንዳንዳቸው 10 ነጥቦችን በመሰብሰብ የምድባቸው አላፊ ኾነዋል።
ቀሪ ሁለት የዚህ ምድብ ጨዋታዎችም ከመርሐ ግብር ማሟያነት የዘለለ ሚና አይኖራቸውም።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here