ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ከጥቅምት ስምንት ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ይካሄዳል። የ2024 አህጉር አቀፍ የእጅ ኳስ ሻምፒና ውድድር ደግሞ በጥቅምት ወር መጨረሻ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ሁለቱን ስፖርታዊ ኹነቶች በተመለከተ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ፣የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌደሬሽን እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ መሰል መድረኮች ከውድድር ባለፈ ለሀገራችን በርካታ እድሎችን ይዘው የሚመጡና ገጽታ ግምባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው ብለዋል። በእነዚህ መድረኮች የሀገር ገጽታ ግምባታ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥም ተጠቁሟል። ከገጽታ ግምባታ በተጨማሪ በሀገራችን የሚካሄዱ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ መድረኮች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መኾናቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የካፍ ጠቅላላ ጉባኤን ጨምሮ አህጉር አቀፍ የእጅ ኳስ ሻምፒዮናን በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተሠሩ መኾኑንም ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደ ሰንበት(ዶ.ር) የውድድሩ በሀገራችን መካሄድ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት እና ስፖርቱ ላይ መነቃቃት ለመፍጠር ሚናው ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ ከ350 በላይ ልዑካን ተሳታፊ እንደሚኾኑም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ደግሞ በ46ኛው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ከ400 በላይ ልዑካን እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። መንግሥት በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለው ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ፍላጎቱ እውን እንዲኾን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የጉባኤው በሀገራችን መደረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ሀገራችን ለማምጣት ግን የካፍና የፊፋ መመዘኛዎችን የሚያሟሉ ስታዲየሞች ሊኖሩ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በቀጣይ አዲስአበባና አደይ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ በየክልሉ የተጀመሩ ስታዲየሞችን ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!