ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢትዮጵያዉያን አባት እና እናት በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት የተወለደችው ናኦሚ ግርማ የቢቢሲ የ2024 የዓመቱ ምርጥ የሴት እግር ኳስ ዕጩ ተጫዋች ኾና ቀርባለች፡፡ ቢቢሲ የመጨረሻዎቹ አምስት የዓመቱ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ያላቸው ባርባራ ባንዳ፣ አይታና ቦንማቲ፣ ናኦሚ ግርማ፣ ካሮላይን ግርሃም ሃንሰን እና ሶፊያ ስሚዝ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያውያኑ ቤተሰቦቿ በአሜሪካ የተወለደችው የ24 ዓመቷ ናኦሚ ግርማ የአሜሪካው ሳን ዲያጎ ዌቭ ክለብ ተጫዋች ናት፡፡ ባለፈው ጥር ወር የአሜሪካ የሴት እግር ኳስ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብላ የተመረጠችው ናኦሚ ግርማ፣ ተከላካይ ተጫዋች ኾና ይህን ክብር ያገኘች የመጀመሪያዋ ተጫዋችም ኾናለች፡፡
ከአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያን ያሸነፈችው ናኦሚ ከክለቧ ሳን ዲያጎ ዌቭ ጋርም የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡ የዩናይትድ ስቴት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኤማ ሄይስ “እንደ እሷ ዓይነት ምርጥ የመሐል ተከላካይ በሕይወቴ ዓይቼ አላውቅም” ስትል ናኦሚን አወድሳታለች፡፡
የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋቾች የሚመረጡት በአሠልጣኞች፣ በተጫዋቾች፣ በእግር ኳስ አሥተዳዳሪዎች እና በጋዜጠኞች መኾኑን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!