ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ጋር የሚያደርገውን ሦስተኛ ጨዋታ ነገ በ02/2017 ዓ.ም ምሽት 1:00 ሰዓት ላይ በአቢጃኑ ስታድ ደ ኢቢምፔ ስታዲየም ያካሂዳል፡፡ ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም ደግሞ ሁለቱ ቡድኖች ምሽት 4:00 ሰዓት ላይ በተመሳሳይ ስታዲየም አራተኛ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የካፍ መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከታንዛኒያ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀች ሲኾን በሁለተኛ ጨዋታዋ ደግሞ በዴሞክራቲክ ኮንጎ የ2 ለ 0 ሽንፈትን አስተናግዳለች፡፡ ጊኒ ከዚህ በፊት ያደረገቻቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች ተሸንፋ የምድቡ ግርጌ ላይ የምትገኝ ሲኾን ኢትዮጵያ ደግሞ በአንድ ነጥብ የምድቧን ሦስተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡
ጊኒ እና ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዘጠኝ ጨዋታዎች የተገናኙ ሲኾን ጊኒ ስድስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ወስዳለች፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ብቻ ጊኒን የረታቻት ሲኾን በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ነገ ምሽት 1:00 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ 10ኛ ጨዋታቸው ኾኖ ይመዘገባል፡፡
ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ እና ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድም ግብ በተቃራኒዎቿ መረብ ላይ ማሳረፍ አልቻለችም፤ በአንጻሩ ሁለት ግቦችን አስተናግዳለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በብሔራዊ ቡድናቸው ውስጥ ግብ ማስቆጠር የሚችሉ አጥቂዎችን ማግኘት እንዳልቻሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አሠልጣኙ በሀገሪቱ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ሳይቀር ግብ በማስቆጠር የሚታወቁት የሌላ ሀገር ተጫዋቾች መኾናቸውንም በጋዜጣዊ መግለጫቸው አሳውቀዋል፡፡ ወደ አይቮሪኮስት ከተጓዙት የዋሊያዎቹ ሥብሥብ ውስጥ ቢኒያም በላይ በጡንቻ መሳሳብ ጉዳት በሁለተኛ ቀን ልምምዳቸው ላይ አለመገኘቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
በጊኒ በኩል የተገለጸ የጉዳት ዜና የለም፡፡ በሁለቱ ቡድኖች ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች የተሻለ የማሸነፍ ግምት የተሰጣቸው ጊኒዎች ናቸው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!