የጋምቢያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከአውሮፕላን አደጋ ተረፉ፡፡

0
474

ባሕር ዳር: ጥር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ኮትዲቯር እያቀና የነበረው የጋምቢያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የተሳፈሩበት አውሮፕላን የኦክስጂን አቅርቦቱ በመቋረጡ ነው አደጋው የተከሰተው። ይሁን እንጅ ተጫዋቾቹ መትረፋቸውን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡

አውሮፕላኑ ከዋና ከተማዋ ባንጁል ተነስቶ ወደ ኮትዲቯር ዘጠኝ ደቂቃ ከበረረ በኋላ የኦክስጂን አቅርቦቱ በመጥፋቱ አብራሪው በድንገት የአውሮፕላኑን አቅጣጫ ቀይሮ ባንጁል አየር ማረፊያ ለማሳረፍ ተገዷል፡፡

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሳይዲ ጃንኮ በኢንስታግራም ገጹ ላይ “32 ሰዓታት ከሳዑዲ አረቢያ (የስልጠና ካምፕ) ወደ ጋምቢያ -ኢስታንቡል – ካዛብላንካ ከዚያም ወደ ኮትዲቯር እየበረርን በነበረበት ቅጽበት የኦክሲጂን አቅርቦት ጠፋ ብሏል፡፡

ወዲያውም በኀይለኛ ራስ ምታት እና በከፍተኛ የማዞር ስሜት እየተሰቃየን ነበር ” በማለት አስፍሯል፡፡ ጃንኮ የቡድን አባላቱ ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ መስልም አጋርቷል፡፡

የጋምቢያ ብሔራዊ የእግር ኳስ አሠልጣኝ ቤልጄማዊው ቶም ሴንትፊየት እንደተናገሩት “ሁላችንም ልንሞት እንችል ነበር” በማለት በአብራሪው ንቃትና ቅልጥፍና በተዓምር በሕይዎት መትረፋቸወን ተናግረዋል፡፡

የጋምቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ “ጊንጦቹን ይዞ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያመራው ቻርተርድ አውሮፕላን በቴክኒክ ችግር ምክንያት ወደ ባንጁል ተመልሷል” ብሏል።
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋምቢያ በምድብ ሦስት ከካሜሩን፣ ሴኔጋል እና ጊኒ ጋር ተመድባለች።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here