ባሕር ዳር: መስከረም 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጀርመናዊው የቀድሞው የሊቨርፑል አሠልጣኝ የሬድ ቡል ግሎባል ሶከር ኀላፊ ኾነው ከጥር 1/2025 (ከአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት) ጀምሮ ኀላፊነታቸውን እንደሚረከቡ ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
የ57 ዓመቱ ጀርመናዊ በቀዮቹ ቤት እጅግ ተዋዳጅ እና ውጤታማው አሠልጣኝ ቢኾኑም የአሠልጣኝነት መንበራቸውን ለኸርኔ ስሎት አስረክበው ያለ ሥራ ከተቀመጡ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
ሊቨርፑሎችን ከ30 ዓመታት በኋላ ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ጋር ያስታረቁት የርገን ክሎፕ በሬድ ቡል ግሎባል ሶከር ኀላፊነታቸው አሠልጣኝነትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡
ክሎፕ በአዲሱ ሥራቸው ማሠልጠንን ጨምሮ ክለባዊ ፍልሥፍናዎችን ማራመድ፣ የተጫዋቾች ሥነ ልቦና ግንባታ፣ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም እና አዳዲስ አሠልጣኞችን የመቅጠር ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሬድ ቡል ግሎባል ሶከር በጀርመን ቡንደስሊጋ የአርቢ ሌዝቢዥ፣ የኦስትሪያው ሬድ ቡል ሳልስበርግ፣ የኒውዮርኩ ሬድ ቡል እና የብራዚሉን ሬድ ቡል ብራጋንቲኖ በሥሩ የያዘ መኾኑንም ስካይ ስፖርት በዘገባው አመላክቷል፡፡
የርገን ክሎፕ በሊቨርፑል በነበራቸው የዘጠኝ ዓመታት ቆይታ ሻምፒዮንስ ሊግን በ2019 እና የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ደግሞ በ2019/20 እ.ኤ.አ. ማሳካታቸው አይዘነጋም፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!