“በውጤት ደረጃ አሁን ያለንበት ሕዝባችን ለእግር ኳሱ ያለውን ፍላጎት እና ፍቅር የሚመጥን አይደለም” የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ

0
237

አዲስ አበባ: መስከረም 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። ጉባኤውን የከፈቱት የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ የተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም በርካታ ሥራዎች የተሠሩበት እና የተሻለ አፈፃፀም የታየበት ነበር ብለዋል።

ተቋርጦ የነበረውን የካፍ የአሠልጣኞች ሥልጠና ማስቀጠል እና ክለቦች ከልማዳዊ አሠራር እንዲወጡ የክለብ ላይሰንሲንግን ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ ሴቶች እና ወጣቶች እግር ኳስ ልማት ላይ ፌዴሬሽኑ በትኩረት ሠርቷል ብለዋል። የክለብ ላይሰንሲግን ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ውስጥ በተወሰኑ ክለቦች በኩል ትክክለኛ እና በቂ መረጃን አለመስጠት እና አዳዲስ አሠራሮችን ያለመቀበል ችግር መታየቱንም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል።

የካፍ እና የፊፋ መመዘኛዎችን የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጀትን ጨምሮ በርካታ ዋጋዎችን እየከፈለ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በውጤት ደረጃ አሁን ያለንበት ሕዝባችን ለእግር ኳሱ ያለውን ፍላጎት እና ፍቅር የሚመጥን አይደለም ብለዋል። ከስታዲየም ጋር በተያየዘ ሁኔታዎች በዚ የሚቀጥሉ ከኾነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በርካታ ውድድሮችን ለመሰረዝ እንደሚገደድም ገልጸዋል።

በኢፌዴሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም አለመኖር የእግር ኳሱ መሠረታዊ ችግር መኾኑን አንስተዋል። በየክልሉ ተጀምረው ግምባታቸው የቆሙ ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑንም አንባሳደር መስፍን ቸርነት ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም እና የአደይ አበባ ስታዲየምን ለማጠናቀቅም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃብት መድቦ እየሠራ ነው ተብሏል። ዛሬ ሙሉ ቀን በሚቀጥለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የ2016 ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ተደርጎበት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here