ተራማጁ አትሌት ምስጋና ዋቁማ!

0
214

አዲስ አበባ: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያንን እንደ ድሮው ያላስደሰተ፤ ከዓለም ድንቅ ሰዓት የያዙ አትሌቶቻችን በኦሊምፒክ መድረክ ግን እንደተጠበቁት ያልተገኙበት ሆኖ አልፏል።

ከታሳታፊ ይልቅ የኦሎምፒክ እና አትሌቲክስ መሪዎች እና ዘመዶቻቸዉ ቁጥር የላቀበት ነበር እየተባለም ብዙ ወቀሳ ተስተናግዶበታል። አሠልጣኝ የሚያሠለጥናትን ልጁን ፍጻሜ ከጎን ኾኖ መከታተል ሲገባው በቲቪ መስኮት ብቻ እንዲመለከት የተገደደበትም ነበር። በብዙ መንገድ በርካታ ብልሹ አሠራር እና ሀገርን የማይመጥን ተግባራትን ባስመለከተን ዉድድር ተስፋ የሰጡን ሰዎችም በጥቂቱ አይተንበታል።

ከነዚህ መካከል ደግሞ ተራማጁ አትሌት ምስጋና ዋቁማ አንዱ ነበር። አትሌት ምስጋና በፓሪስ ኦሊምፒክ ሀገሩን በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ዉድድር ወክሎ አረንጎዴ ፣ቢጫ እና ቀይ ሰንደቁን ከፍ ለማድረግ ታግሏል። በዉድድሩ በብዙ ፈተና ታጅቦም ስድስተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነዉ።

ምስጋና በዉድድሩ ወቅት ዉኃ የሚሠጠዉ እንኳን አጥቶ በሕመም ዉስጥም ሆኖ ያነገበዉን ዓላማ አልረሳም ነበር። በትልቁ መድረክ ሀገርን መወከሉ ደስታን እንዳጎናጸፈዉ እና ክብር እንዲሰማው ማድረጉን ከአሚኮ ጋር በነበረዉ ቆይታ ተናግሯል።

ምስጋና ዉድድሩ ላይ የገጠመዉ ሕመም ከዉኃ ጥሙ ጋር ቢደማመርበትም ከመራመድ ግን አልገታዉም ነበር። ዜሮ ብሎ የጀመረዉ ዉድድር አንድ…ሁለት…አስር እያለ በርምጃዉ ማቆራረጡን ተያይዞታል። ምስጋና በዉድድሩ ስላስመዘገበዉ ዉጤት እና ፉክክር ሲናገር ዉድድሩ እና ተወዳዳሪዎች አልፈተኑትም ነበር ።

“በወቅቱ ሀሳቤ የነበር ለሀገሬ ሜዳሊያ ማስገኘት ነበር፤ ሆኖም በዉድድሩ ወቅት የገጠመኝ ሕመም ውድድሩን ባሰብኩት ልክ እንዳከናዉን አላስቻለኝም፤ ሕመም ባያጋጥመኝ ኖሮ ከዚህ የተሻለ ዉጤት ማምጣት እችል ነበር” ብሏል አትሌቱ።

አትሌት ምስጋና “የእኔ ዉጤት ሌሎች ታዳጊዎችን የሚያነሳሳ ነዉ፤ እኔ ታላላቆቼን አይቼ በድፍረት ወደዚህ ስፖርት ገብቻለሁ፤ አሁን እኔን እያዩ ብዙዎች ወደ ስፖርቱ ብቅ እንደሚሉ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲልም ተናግሯል።

አትሌቱ ፓሪስ ላይ ያስመዘገበዉ ዉጤት እና በችግርም ዉስጥ ሆኖ ያሳየዉ ብቃት ኢትዮጵያ ሁሌም ውጤታማ ነኝ ከምትልበት ሩጫ ባለፈ በመድረኩ በሌሎች ዘርፎችም የዉድድር እድል እንዲገኝ መሥራት እንዳለብን ማሳያ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚመለከተዉ ሁሉ በዚህ የስፖርት ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይኖርበታል።

አትሌት ምስጋና በቀጣይም በዘርፉ ሀገሩን ለማስጠራት ጠንክሮ እንደሚሠራ ከአሚኮ ጋር በነበረዉ ቆይታ ተናግሯል። በዉድድሩ 20 ኪሎ ሜትሩን 1:19:13 በኾነ ሰዓት ጨርሶ የኢትዮጵያን ክብረ ወሰን በእጁ ይዟል።

ይህ አትሌት በተከናወነዉ የመላዉ አፍሪካ ጨዋታዎች ለሀገሩ ወርቅ ማምጣቱም የሚታወስ ነዉ። በብዙ ዉዝግብ ዉስጥ ባለፈው የፓሪሱ ኦሊምፒክ የተገኘ የወደፊት የኢትዮጵያ የእርምጃ ዉድድር ተስፋም ነው ምስጋና ዋቁማ።

ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ኃይለየሱሥ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here