በፓሪስ ኦሎምፒክ ለተሳተፉ አትሌቶች እና የልዑካን ቡድን አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

0
213

ባሕር ዳር: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም በፈረንሳይዋ ፓሪስ ከተማ ሲከናወን በቆየው የኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በውኃ ዋና፣ እርምጃ እና የሩጫ ውድድሮች ተሳትፉለች። በውድድሩም ኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ ብቸኛውን ወርቅ ያስገኘ አትሌት ነው።

ትዕግስት አሰፋ፣ ጽጌ ድጉማ እና በሪሁ አረጋዊ ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል። ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰው የኢትዮጵያ ልዑክ አቀባበል ተደርጎለታል። በቦታው በመገኘትም የኢዮጵያ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፣ በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የጤና ማኅበራዊ ባሕል እና ስፖር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ፣ በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ድኤታዎች ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በአቀባበል ሥነ ስርዓቱ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። በውዝግብ በተሞላው የፓሪስ ቆይታ ኢትዮጵያ በተጠበቀው ልክ ዉጤት አለማምጣቷ ብዙዎችን ያስከፋ ኾኖ አልፏል። የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) እንደ ሀገር የተመዘገበው ውጤት አመርቂ አለመኾኑን አንስተው ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን የሌላት መኾኑ ስፖርቱ ላይ ትልቅ ፈተና እንደኾነ አንስተዋል።

በውድድሩ የተሳተፉ አትሌቶችም በፓሪስ የነበረው ቆይታ በታሰበው ልክ አለመኾኑን አንስተው ስለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ፓሪስ ላይ በተደረገው 33ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በአንድ ወርቅ እና ሦስት ብር ከዓለም 47ኛ ከአፍሪካ ደግሞ አራተኛ ኾና አጠናቅቃለች።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here