በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ዛሬ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ይደርጋሉ፡፡

0
265

ባሕር ዳር:ጥር02/2016ዓ.ም(አሚኮ)በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ዛሬ ኢትዮጵያ መድን ከድሬድዋ ከተማ እና ባሕርዳር ከተማ ከሀምበሪቾ ይጫወታሉ። ዛሬ 9 ሰዓት ኢትዮጵያ መድን ከድሬዳዋ ከተማ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ መድን ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኝ ነጥብ በመያዝ እና በሦስት የግብ ዕዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የመድን ቡድን የግብ ማስቆጠር ችግር ጎልቶ ይታይበል። ከሦስተኛው እስከ ስድስተኛው ሳምንት ድረስ በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ግብ አለማስቆጠሩ አብነት ይኾናል፡፡ ስለኾነም አሠልጣኙ ግብ ማስቆጠር የሚችል የአጥቂ አማራጮችን ማፈላለግ ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና በአንጻሩ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቡድኑ በተሻለ መንገድ የመከላከል አቅም አለው፡፡
በጨዋታው መድን ጉዳት ምክንያት ሀቢብ ከማልን አያሰልፍም ተብሏል።

ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በዘጠኝ ጨዋታ በስምንት ነጥብ እና በአራት የግብ ዕዳ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ብርቱካናማዎቹ በፋሲል ከነማ ሦስት ግቦችን አስተናግደው በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ የመከላከል ድክመታቸው በግልጽ ታይቷል።

አሠልጣኙ ታዲያ ከዚህ ሽንፈት ለማገገምም የተጠቀሰውን ችግር አርመው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት ሳስቶ የነበረውን የማጥቃት ክፍላቸው መጠነኛ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሲን ጀማል ፣ ዓብዱልፈታህ ዓሊ እና ተመስገን ደረስ በጉዳት ምክንያት ቡድናቸውን አያገለግሉም። ባለፈው ጨዋታ ያልተሳተፈው ቻርለስ ሙሴጌ ግን ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ መድን እና ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መድን ስድስት ግብ ሲያስቆጥር ድሬዳዋ አምስት ግብ አስቆጥሯል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ዳንኤል ይታገሱ ይመሩታል፤ ለዓለም ዋሲሁን እና ወጋየሁ አየለ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ባህሩ ተካ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል ። ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ባሕር ዳር ከተማ ከ ሀምበርቾ ዱራሜ ይጫወታሉ፡፡ ባሕር ዳር ከተማ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ተጫውቶ በአስራ ስምንት ነጥብ እና በስድስት የግብ ክፍያ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥር በወጣበት የሻሸመኔ ጨዋታ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ነበር፤ ይሁንና ያገኙትን የግብ ዕድሎች መጠቀም አልቻሉም፡፡
በአማዛኙ ወደ ራሱ የግብ ክልል ቀርቦ ለመከላከል የመረጠውን ተጋጣሚ ለማስከፈት ባሕር ዳሮች ሲቸገሩ ተስተውለዋል። የዛሬው ተጋጣሚያቸውም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ ይከላከላል ተብሎ ስለሚጠበቅ አሠልጣኙ ከወዲሁ መፍትሄ ማበጀት ይኖርባቸዋል።

በባሕር ዳር ከተማ በኩል በመጨረሻው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣው ፍሬዘር ካሳ አይሰለፍም፡፡ አደም አባስ ደግሞ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። በጎው ዜና ደግሞ ከተፈቀደለት የዕረፍት ጊዜ የዘገየው ሱሌይማን ትራኦሬ ቡድኑን ተቀላቅሏል ተብሏል።

ሀምበርቾ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ነጥብ ብቻ በመያዝ እና በ11 የግብ ዕዳ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ በየጨዋታው መከላከል ላይ ያመዘነ የአጨዋወት ስልት ይከተላል፡፡ ኾኖም ተጋጣሚዎቹ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ስለነበራቸው ከሽንፈት አልዳነም፡፡

ቡድኑ በዛሬው ጨዋታም በተመሳሳይ ወደ ራሱ ግብ ክልል በቁጥር በዝቶ የመከላከል አጨዋወት ይከተላል ተብሎ ይገመታል፡፡ የኾነ ኾኖ ቡድኑ በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የማጥቃት ጥምረት የማስተከል ሥራም ከሠሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ የሚጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው።

በሀምበርቾ በኩል በረከት ወንድሙ የመሰለፍ ኹኔታው አጠራጣሪ ነው። ቅጣቱን የጨረሰው ቴድሮስ በቀለ ግን ወደ ሜዳ ይመለሳል። ሶከር ኢትዮጵያ እንደዘገበው ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በመሐል ዳኝነት፣ ሙሉነህ በዳዳ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ሚካኤል ጣዕመ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን እንዲመሩ ተሰይመዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here