ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርብ ምሽት 4፡00 ሰዓት ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ለዋንጫ፣ ለአውሮፓ መድረክ እና ከፕሪምየር ሊጉ ላለመውረድ ከፍተኛ ፍልሚያ ያደርጋሉ፡፡ ክለቦቹ ውጤታማ ለመኾን አዳዲስ ተጨዋቾችን በውድ ዋጋ ከማስፈረማቸው ባለፈ የአካዳሚ ተጨዋቾቻቸውን በማሳደግ ለተሻለ ውጤት ሲጥሩም ይስተዋላሉ፡፡
በአካዳሚ ተጨዋቾች ውጤታማ በመኾን የቀድሞውን የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን የሚስተካከላቸው ያለ አይመስልም፡፡ ፈርጉሰን በአንድ ዓመት አምስት ታዳጊ ተጨዋቾችን በዋናው ቡድን በማሰለፍ ውጤታማ ኾነዋል፡፡ ”ፈርጌ ቤቢስ” በመባል የሚታወቁት ዴቪድ ቤካም፣ ፊል ኔቭል፣ ጋሪ ኔቭል፣ ኒኪ በት እና ፖል ስኮልስ በታዳጊነታቸው ዋናውን ቡድን ተቀላቅለው ለዓመታት ውጤታማ መኾን የቻሉ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ አካዳሚ አላቸው የተባሉት ቼልሲ፣ ሳውዝአምፕተን፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በአካዳሚ ውጤቶቻቸው ተጠቃሚዎች ስለመኾናቸው የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግም ከአካዳሚ ወጥተው በዋናው ቡድን ውስጥ ለውጤት የሚጠበቁ ተጨዋቾችን ቢቢሲ ዘርዝሯቸዋል።
የ17 ዓመቱ ትሮይ ኒዮሪ በሊቨርፑል ዋናው ቡድን ውስጥ በአማካይ ሥፍራ ተጽዕኖ ይፈጥራል ተብሎ በአሠልጣኝ አርኔ ስሎት ታምኖበታል፡፡ ቼልሲ በክረምቱ በአሜሪካ ባደረጋቸው የዝግጅት ጨዋታዎች ላይ ጆሽ አቺምፖንግን ከአካዳሚው ወስዶ ተጠቅሞበታል፡፡ አቺምፖንግ የመሀል እና የቀኝ ክንፍ ተከላካይ ኾኖ መጫወት የሚችል ተጫዋች ነው፡፡
የ16 ዓመቱ የፊት አጥቂ ሚኬይ ሙር በቶተንሃም ሆትስፐሮች አሠልጣኝ ኤንጂ ፖስትኮግሉ ታምኖበት ከአካዳሚያቸው የዋናው ቡድን ተጨዋች ተደርጓል፡፡ ቶተንሃሞች በውሰት ካለቀቁት በቀር የአጥቂነት ተሰጥኦውን ሊያሳይ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የ17 ዓመቱ የአርሰናል የአማካይ ተጨዋች ኢታን ንዋኔሪ ባለፈው ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ ጨዋታ ተሰልፏል፡፡ የአርሰናሉ አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ የንዋኔሪ እና ሌሎች ታዳጊ ተጨዋቾች በዋናው ቡድን የመሰለፍ ዕድል በራሳቸው ጥረት የሚወሰን ነው ብለዋል፡፡
ከአርሰናል አካዳሚ ወጥቶ ማንቸስተር ዩናይትድን የተቀላቀለው ታዳጊው የፊት መስመር ተሰላፊ ቺዶ ኦቢ ማርቲን ሌላኛው ተጠባቂ ነው። የአርሰናል ታዳጊ ቡድን ውስጥ ምርጥ አጥቂነቱን ያስመሰከረ በመኾኑ በማንቸስተር ዩናይትድ መለያ ምን ተዓምር እንደሚያሳይ ተጠባቂ ነው፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ አሁንም ድረስ በአካዳሚ ፍሬዎቹ ተጠቃሚ ለመኾኑ እንደማሳያ የሚወሰደው ደግሞ የ18 ዓመቱ ኮቢ ማይኖ ነው፡፡
ሮድሪን የመሳሰሉ ድንቅ አማካዮች ባሉበት የማንቸስተር ሲቲ ዋናው ቡድን ውስጥ በቋሚነት መሰለፍ አስቸጋሪ ቢመስልም የ19 ዓመቱ ኒኮ ኦሪዬሊ በፔፕ ጋርዲዮላ የሚሰጠውን ዕድል ሁሉ በአግባቡ በመጠቀም አቅሙን ለማሳየት ተዘጋጅቷል፡፡ እነዚህ እና ሌሎችም የአካዳሚ ፍሬዎች በየክለቦቻቸው የሚሰጣቸውን እድል ተጠቅመው በፕሪምየር ሊጉ የሚያሳዩት ብቃት ይጠበቃል። በታዳጊ ተጨዋቾች አቅም እና ክህሎት በሚያምኑ አሠልጣኞች ዕድላቸውም እንዲሁ ይወሰናል።
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



