በትናንት ስንካሰስ ለነገም እንዳንሰንፍ!

0
228

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 33ኛው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። በ16 ከተሞች በተዘጋጁ 39 ምርጥ የመወዳደሪያ ቦታዎች ከ206 ሀገራት የተወከሉ 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮችን አካሂደዋል።

የተለያዩ ሀገራትን እና ተቋማትን የወከሉ 20 ሺህ ጋዜጠኞች ፓሪስ ከትመው ውድድሮችን በቀጥታ ዘግበዋል። 45 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ደግሞ የበጎ አድራጎት ተግባር አከናውነዋል። ከ45 ሺህ በላይ የጸጥታ ኃይሎች ውድድሮች በሰላም እንዲጠናቀቁ ዘብ በመቆም ግዴታቸውን ተወጥተዋል። በውድድሩ መክፈቻ ዕለት በባቡር ሐዲዶች ላይ ፍንዳታ ደርሶ መንገደኞች ለሰዓታት መስተጓጎላቸው ግን ብዙዎችን አስደንግጦ ነበር።

ፈረንሳይ ለዚህ ኦሊምፒክ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በጀት ፈሰስ አድርጋለች። ከ4 ቢሊዮን በላይ የዓለም ሕዝብም ውድድሮችን ተከታትሏል ነው የተባለው። ይህ የፓሪስ ኢሊምፒክ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ምሽት 4፡ዐዐ ሰዓት አካባቢ 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ደ ፍራንስ ስታዲየም በድምቀት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያም በፓሪሱ ኦሎምፒክ 38 ስፖርተኞችን አሳትፋ በወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ ብቻ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። በሪሁ አረጋዊ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች፣ ፅጌ ዱጉማ በ800 ሜትር እና ትዕግስት አሰፋ በማራቶን የብር ሜዳሊያ ማምጣታቸው ሳይዘነጋ ማለት ነው። እናም ኢትዮጵያ በአራት ሜዳሊያዎች ከዓለም 45ኛ ደረጃን በመያዝ ነው ያጠናቀቀችው።

ቢቢሲ፣ ፍራንስ 24፣ ዴይሊ ሜይል እና ሌሎች ትልልቅ የመገናኛ አውታሮች የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ያስመዘገበው ውጤት አነስተኛ መኾኑን ተቀባብለውታል። በተጨማሪም ከማራቶን በስተቀር የተሳታፊ አትሌቶች የማሸነፍ ወኔ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ተዳክሞ ታይቷል ሲሉ ዘግበዋል፡፡ ነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት እየቻሉ ባጨራረስ ድክመት እና መፋዘዝ ውጤቱን ለሌሎች ሀገራት አሳልፈው የሰጡ አትሌቶችም መታየታቸውን ተመልክተናል። ይህ ደግሞ ሀገርን ካለመመልከት፣ ሕዝብን ካለማንገስ እና ለሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለት ካለመጨነቅ የመጣ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ይሄው ዘገባ በኢትዮጵያም ኾነ ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩ ጋዜጠኞችን እና የስፖርት ባለሙያዎችን ሐሳብ ያካተተ ነው። ከመጀመሪያው አንስቶ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ኦሎምፒክ ቡድን ምርጫ ፍትሓዊ እና ብቃት ላይ ያተኮረ ሳይኾን በግለሰቦች ይሁንታ የተመሠረተ ነው ባዮች ተደምጠው ነበር።

ለአብነትም የ23 ዓመቷ የፍሬወይኒ ኃይሉ በ1ሺህ 500 እና በ5 ሺህ ሜትር ከሦስት ወራት በፊት በግላስኮ በተካሄደው ውድድር ወርቅ ማምጣቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በ5 ሺህ ሜትር ደግሞ የዓመቱ ሦስተኛ ፈጣን ሰዓትም ባለቤት ናት። ይህች አትሌት ታዲያ ኹሉንም የመምረጫ መመዘኛ በማሟላቷ በ5 ሺህ ሜትር እንድትሮጥ ተወስኖ እንደነበር የስፖርት ዘጋቢዎቹ ያስታውሳሉ፡፡

ጉዳፍ ጸጋየ ደግሞ በሁለት ርቀቶች ብቻ እንድትሳተፍ ፌዴሬሽኑ መወሰኑን መረጃዎች ተሰራጭተው ነበር። ይሁንና አሳማኝ ባልኾነ ኹኔታ ፍሬወይኒ ተጠባባቂ ኾና ጉዳፍ በሦስት ርቀቶች እንድትወዳደር በመደረጉ ውጤት ከኢትዮጵያ እጅ እንዲወጣ ተደርጓል ባዮች እንዲበራከቱ ምክንያት ተፈጥሯል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር በሌሎች ርቀቶችም ተስተውሏል ባይ ናቸው አስተያዬት ሰጪዎች፡፡

“ስለዚህ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ለውጤት መጥፋት እና ለዘርፉ ውድቀት ኃላፊነቱን ከመውሰድ ባለፈ ተጠያቂ ሊኾን ይገባዋል” የሚሉ ድምጾችም ተበራክተዋል፡፡ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና የአትሌቲክስ አሠልጣኝ መሠረት መንግሥቱ በፓሪስ የአትሌቲክስ ቡድን የተመረጠው’ “በእከክልኝ ልከክልህ” እንጅ በወቅታዊ ብቃት እና ልምድ አልነበረም ነው ያሉት።

መምህሩ ምሳሌ ሲያስቀምጡም በወንዶች ኦሊምፒክ በቀጥታ እንዲወዳደሩ የተመረጡት አትሌት ሲሳይ ለማ፣ ዴሬሳ ገለታ እና ቀነኒሳ በቀለ ነበሩ ብለዋል። ታምራት ቶላ በማራቶን እንዲወዳደር የተመዘገበው በተጠባባቂነት እንደነበር አስታውሰዋል።ነገር ግን የመጀመሪያ ተመራጭ የነበረው ሲሳይ ‘ከእኔ ይልቅ ታምራት ቢወዳደር ውጤት ይመጣል’ በሚል ወስኖ ከውድድሩ መውጣቱን ተናግረዋል።

ሲሳይ እና ታምራት በገዛ ፈቃዳቸው “ከእኔ ይልቅ አንተ ብትወዳደር ውጤታማ ትኾናለህ” የሚለው ትርፋማ ሐሳብ የኦሊምፒክ ኮሚቴውን የአትሌቶች ምርጫ የጨረባ ተስካርነት የገለጠ ነው ሲሉ ምሁሩ አብራርተዋል። የእነ ታምራት መቀያዬር (ይህ በመኾኑም) በውጤት ድርቅ የተመታውን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ውጤት በመጠኑ አስታግሷል። ታምራት ቶላም ለቢቢሲ“አትሌት ሲሳይ ለእኔ ይሄ የፓሪስ ውድድር ይቀርብኝ፤ አንተ ብትወዳደር የተሻለ ነው ብሎ ነው ቦታውን የለቀቀልኝ” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ነገር ግን ምርጫው በወቅታዊ ብቃት፣ በችሎታ፣ አቅም፣ ልምድ መሠረት ያደረገ እንዳልነበር መምህር መሠረት ተናግረዋል። ይህ ዓይነቱ የተዝረከረከ አሠራር እና የማናለብኝነት ባሕርይ ደግሞ “በእንቁላሉ” ካልታረመ ነገ ያውም አድማሱን አስፍቶ እነ አበበ ቢቂላ፣ ምሩጽ፣ ማሞ፣ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ ደራርቱ፣ ጥሩነሽ፣ መሠረት ፣አልማዝ እና ሌሎችም አሸንፈው ከፍ ከፍ ያደረጓትን ስመ ገናና ሀገር፣ ሰንደቅ ዓላማ እና ሕዝብ ዝቅ የማያደርጉበት ምክንያት የለም ሲሉ መክረዋል።

መምህር መሠረት አያይዘውም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በሰላም ወደ ሀገር ቤት እንዲመለስ ተመኝተው “ላለፈ ክረምት ቤት ባይሠራም” በመጭው ክረምት በዝናብ ላለመበስበስ ከወዲሁ ጥሩ ቤት መሥራት እንደሚገባው ኹሉ ከአትሌት መረጣ እስከ ውድድር በነበረው ሂደት ዙሪያ የምር ስለሀገር እና ሕዝብ ክብር ተብሎ መወያዬት ግድ ይለናል ነው ያሉት።

ተነጋግረንም ችግር ፈጣሪውን በመጠየቅ፣ ምስጉኑን በማወደስ፣ ለችግሮቹ ሳይንሳዊ የመፍትሔ ሐሳብ በማስቀመጥ በሎስ አንጀለስ ለሚዘጋጀው የ2028ቱ ኦሎምፒክ ከወዲሁ መዘጋጀት አለብን ብለዋል። “ትናንት የእኛ ተፎካካሪዎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አትሌቶች ነበሩ። ዛሬ ግን የእኛ አትሌቶች በነጮች ተወረዋል። ስለዚህ የበላይነት ክብራችንን ለመመለስ ዛሬ መሥራት ካልጀመርን ነገ ውድድር ላይ ውጤት ከሰማይ አይወርድምና ነው” ያሉት መምህር መሠረት።

በሰው መለዋወጥ ሳይኾን በሥርዓት የሚመራ አስተሳሰብ መገንባት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ሁሉም አካላት ለለውጥ መሥራት አለባቸው፤ የዚህ ችግር ዋነኛ ተዋንያንም ተጠያቂ መኾን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። “ለቆሸሸ ሸሚዝ ኮሌታ እያጠቡ መኖር መቆም አለበት፤ እድፍ ተሸካሚውን የሰውነት ክፍል በደንብ ማጽዳት ተገቢ ነው” ሲሉ የስፖርት ባለሙያው መክረዋል።

የፈረንሳዩን ኦሎምፒክ መልሰን ማገኘት አንችልም። ከዛሬው ጉደለት ከተማርን እና በቁጭት ከሠራን የሎስ አንጀለሱ ድግስ ቅርብ ነው። ስለዚህ በትናንት ስንካሰስ ለነገም እንዳንሰፍ መጠንቀቅ የተሻለ ነው። አራት ዓመት ሩቅ አይደለምና።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here