ከውድድር በፊት ቅድሚያ ለኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የሚሰጠው 10 ሺህ ሜትር።

0
296

ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሎምፒክ ውድድሮች የፓሪሱን ሳይጨምር 58 ሜዳሊያዎችን ሠብሥበዋል፡፡ ከተገኙት ሜዳልያዎች መካከል አብዛኞቹ በ10 ሺህ ሜትር የተገኙ ናቸው። በተለይ በሴት 10 ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ውድድሮች እስካሁን ድረስ 11 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 5 የወርቅ፣ 2 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች በኢትዮጵያውያኑ ሴት አትሌቶች በ10 ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ውድድሮች የተመዘገቡ ድሎች ናቸው፡፡ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በ1992 ባርሴሎና ላይ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ በማስገኘት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አትሌት ናት፡፡
ደራርቱ በ2000 የሲድኒው ኦሎምፒክም ለራሷ እና ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ስታስገኝ በወቅቱ ያስመዘገበችው ሰዓትም የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ነበር፡፡

ጥሩነሽ ዲባባ በ2008 ቤጂንግ ላይ በ10 ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ክብረ ወሰንን በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳሊያን አግኝታለች፡፡ በ2012 ለንደን ኦሎምፒክ ላይ ሌላኛውን የኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በጥሩነሽ ተመዝግቧል። አልማዝ አያና በ2016 ሪዮ ዴጄኔሮ ላይ የዓለም የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰንን በማሻሻል ጭምር ድል አድርጋለች፡፡

ጌጤ ዋሚ በ2000 ሲድኒ እንዲሁም እጅጋየሁ ዲባባ በ2004 በአቴንስ ኦሎምፒኮች በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች ለሀገራቸው የብር ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ናቸው፡፡ ጌጤ ዋሚ 1996 አትላንታ፣ ደራርቱ ቱሉ 2004 አቴንስ፣ ጥሩነሽ ዲባባ 2016 ሪዮ ዴጄኔሮ እና ለተሰንበት ግደይ በ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ለሀገራቸው እና ለራሳቸው የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል፡፡

እናም በኦሎምፒክ ታሪክ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር የኢትዮጵያን ያህል የደመቀ ታሪክ ያለው ሀገር የለም። ርቀቱ በተነሳ ቁጥርም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ቀድመው ይነሳል። የፓሪሱ ኦሎምፒክ 10 ሺህ ሜትር ውድድር ዛሬ ይከናወናል። በርቀቱ በልጆቿ የገዘፈችው ኢትዮጵያም ዛሬ የናፈቃትን ወርቅ ትጠብቃለች። ትናንት በደራርቱ፣ ጥሩነሽ እና ሌሎች ከፍ ብሎ የተውለበለበው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩ ባንዲራ ዛሬም በተተኪዎቹ ከፍ እንዲል ይጠበቃል። ጉዳፍ ጸጋይ፣ ጽጌ ገብረሰላማ እና ፎትዬን ተስፋይ ደግሞ የአሁኖቹ ደራርቱ እና ጥሩነሽ ለመኾን ተዘጋጅተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here