ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ በወንዶች ማራቶን ለወርቅ ሜዳሊያ ከሚጠበቁት አትሌቶች ውስጥ ቀዳሚውን ግምት የተሰጠው ኬኒያዊው ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ነው፡፡ ኪፕቾጌ ከቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ጋር ባደረገው ቆይታ ለአዲስ የማራቶን ታሪክ እንደሚሮጥ አሳውቋል፡፡
ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ እና የውጤት ፈር ቀዳጁ ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1960 በሮም እና በ1964 በቶኪዮ ኦሎምፒኮች የድል ባለቤት ኾኗል፡፡ ጀርመናዊው ዋልደማር ቺፒኒስኪ በ1976 እና በ1980 እንደ አበበ ቢቂላ ሁሉ በሁለት የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድሮች አሸንፏል። ኬኒያዊው ኢሊዩድ ኪፕቾጌም በ2016 እና በ2020 በቶኪዮ እና በሪዮ ዴጄኔሮ ኦሎምፒኮች አሸናፊ መኾን ችሏል፡፡
በዓለም የኦሎምፒክ ታሪክ በማራቶን ሩጫ ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ ጀርመናዊው ዋልደማር ቺፒኒስኪ እና ኬኒያዊው ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ በጋራ የክብረ ወሰን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ኪፕቾጌ የፓሪስ ሙቀት እና ወጣት የማራቶን ሯጮች ለስኬቱ ፈተና እንደሚኾኑበት ቢገምትም፣ በማራቶን ሩጫ ለሦስኛ ጊዜ በማሸነፍ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ያለውን አቅም ሁሉ እንደሚጠቀም ገልጿል፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው ጥቁሩ አፍሪካዊ ሻምበል አበበ ቢቂላ በኦሎምፒክ ታሪክ የማራቶን የሰዓት ክብረ ወሰን ከማሻሻሉም ባለፈ ሁለት ጊዜ ባለ ድል በመኾን የድርብ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ኾኖም ቆይቷል፡፡ እሁድ በ05/12/2016 ዓ.ም በሚካሄደው የፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ለአሸናፊነት ተገምተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!