ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አትሌት ብርቄ ኃየሎም ዛሬ ከቀኑ 7፡45 ላይ ባደረገችው የ1 ሺህ 500 ሜትር የድጋሚ ማጣሪያ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች፡፡ በ5 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድራቸውን ያደረጉት ሐጎስ ገብረሕይወት፣ አዲሱ ይሁኔ እና ቢኒያም መሐሪም ለፍጻሜ ውድድሩ አልፈዋል፡፡
በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የተወዳደረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብርቄ ኃየሎም ለሁለተኛ ጊዜ ባገኘችው ዕድል በምድብ አንድ 4 ደቂቃ ከ01 ሴኮንድ ከ47 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ወጥታለች። አትሌቷ ትናንት በተካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ 4 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ በመጨረስ 11ኛ መውጣቷ ይታወቃል።
አትሌት ጉዳፍ ፀጋየ እና አትሌት ድርቤ ወልተጂ ትናንት በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ከየምድባቸው አንደኛ በመውጣት በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወሳል። “ሪቸንጅ ራውንድ” በፈረንሳይኛ ትርጉሙ ሁለተኛ ዕድል ሲኾን መሰናክልን ጨምሮ ከ200 እስከ 1ሺህ 500 ሜትር ርቀቶች አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉም ውድድራቸውን ካጠናቀቁ በድጋሚ የማለፍ ዕድል የሚያገኙበት የውድድር አማራጭ ነው፡፡
የሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድሩ ሐሙስ ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ላይ ይደረጋል። ሦስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለፍጻሜ ያለፉበት የወንዶች 5 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ደግሞ ቅዳሜ ነሐሴ 4 / 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ እንደሚካሄድ ከፓሪስ ኦሎምፒክ የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!