ባሕር ዳር: ጥር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ በመዲናዋ አቢጃን በሚገኘው እና 60 ሺህ ተመልካች በሚይዘው በአላሳን ኦታራ ስታዲየም የፊታችን ቅዳሜ ሲደረግ ኮትዲቯር ከጊኒ ቢሳው ይጫወታሉ፡፡ ስታዲየሙ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ተጀምሮ በ2020 ተገንብቶ መጠናቀቁን ካፍ ኦንላይን ዘግቧል፡፡
የአላሳን ኦታራ ስታዲየም እንደ አትሌቲክስ መሮጫ፣ የጉባኤ አዳራሽ፣ የጂም መስሪያ ቴክኖሎጅ፣ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ደኅንነታቸው የተጠበቁ ስፍራዎችም አሉት፡፡
ሁለተኛው ስታዲየም ስታዴ ላፓኢክስ ይባላል፤ በቡዋኬ ከተማ የተገነባ ነው፡፡ 40ሺህ ተመልካች የማስተናገድ አቅምም አለው፡፡
የስታዲየሙ መቀመጫዎች በአረንጓዴ፣ ነጭ እና ብርቱካናማ ቀለም ያጌጡ ናቸው፡፡ ይህም የኮትዲቯርን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የሚወክል መኾኑን ዘገባው አስታውሷል። ሦስተኛው ስታዲየም የፊሊክስ ሁፉዌት ቦዪኒ ስታዲየም አቢጃን ውስጥ ይገኛል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1952 እስከ 1964 ሲገነባ 29 ሺህ ተመልካች እንዲይዝ ተደርጎ ነው፡፡
ነገር ግን ለ34ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ሲባል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2023 የመቀመጫ ወንበሮቹ፣ ሜዳው፣ የመልበሻ ክፍሎቹ እና የእንግዳ መቀበያ ሳሎኖቹ ላይ ሙሉ እድሳት እንዲሁም ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ ተመልካች የመያዝ አቅሙም ወደ 33 ሺህ ከፍ ብሏል፡፡
ስታዲየሙ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ሁፉዌት ቦዪኒ ስም ተሰይሟል፡፡ የሀገሪቱ ሕዝብ ስታዲየሙን “ቅርሳችን” ብለው ይጠሩታል፡፡ ስታዲየሙ ከእግር ኳስ በተጨማሪ አትሌቲክስን እንዲያስተናግድ ኾኖ ነው የተሠራው፡፡
አራተኛው የሎውረንት ቦኩ ስታዲየም በሳን-ፔድሮ ከተማ ይገኛል፡፡ 20 ሺህ ተመልካች ማስተናገድ ይችላል፡፡ ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ ወንበር ተተክሎለታል፡፡ይህ ስታዲየም ለ34ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ተብሎ በአዲስ የተገነባ ነው።
ስታዲየሙ የተሰየመው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 በአፍሪካ ዋንጫ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን 14 ግቦችን ባስቆጠረው ኮትዲቯራዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ላውረንት ቦኩ ነው። ሀገሬው ይህን ተጫዋች “አርበኛው!” በማለት ያወድሰዋል፡፡
አምስተኛው ስታዴየም ቻርልስ ኮናን ባኒ ይባላል፡፡ ያሙሶኩሮ ከተማ ላይ የተገነባ ነው፡፡ በ2022 የተከፈተው ስታዴ ቻርለስ ኮናን ባኒ 20 ሺህ ተመልካች ያስተናግዳል፡፡
ስድስተኛው ስታዲየም የአማዱ ጆን ኩሊባሊ ስታዲየም ነው፡፡ በኮርሆጎ ከተማ የሚገኝ ሲኾን 20 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው፡፡
ስታዲየሙ በሟቹ የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ጎን ኩሊባሊ ስም የተሰየመ ነው፡፡ የካቲት 3/2016 ዓ.ም የዋንጫው ጨዋታ በአላሳን ኦታራ ስታዲያም ይካሄዳል ሲል ካፍ ኦንላይን ዘግቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!