የኢትዮጵያ ወርቅ ሜዳሊያ ዛሬ ይጀምር ይኾን?

0
216

ባሕር ዳር: ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቀደሙት ድንቅ አትሌቶቻችን ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር በ5 ሺህ ሜትር በ2008 ቤጂንግ እና በ2012 ለንደን ኦሎምፒክ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ መኾናቸው ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ የሚጠበቀው የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ውድድር ዛሬ ማምሻውን በስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡

ውድድሩ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ሲካሄድ በፍጻሜው ጉዳፍ ፀጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና መዲና ኢሳ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ። አትሌቶቹ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም የተደረገውን ማጣሪያ አልፈው ለፍጻሜው ደርሰዋል። ውድድሩን ያሸንፋሉ ተብሎ የቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዷ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የኾነችው ጉዳፍ ፀጋየ ናት። ጉዳፍ እ.አ.አ በ2023 በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደ ውድድር 14 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ ክብረ ወሰኑን የጨበጠችበት ሰዓት ነው።

አትሌቷ በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታ ነበር፤ በሁለተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ወርቅ ለማምጣት ትሮጣለች። ሌላኛዋ ተወዳዳሪ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይሄ ሁለተኛ ተሳትፎዋ ነው። እጅጋየሁ በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5 ሺህ ሜትር ፍጻሜ 5ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ ነበር። አትሌቷ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 በአሜሪካ ኢውጅን በተደረገ ውድድር 14 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ ከ98 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በፍጻሜው ኢትዮጵያን የምትወክለው ሦስተኛ አትሌት ታዳጊዋ መዲና ኢሳ ናት፤ መዲና በኦሊምፒክ ስትሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። አትሌት መዲና ከሁለት ዓመት በፊት በለንደን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር 14 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ከ54 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በጋና አክራ በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በተከናወነው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እና ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። በፍጻሜው የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውያኑ ፌዝ ኪፕዬጎን እና ቢትሪስ ቺቤት እንዲሁም በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ ከኾነችው ሲፋን ሀሰን ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት ይጠበቃል።

በተለይም ወጣቷ ኬኒያዊት ኪፕዬጎን ለኢትዮጵያኑ አትሌቶች ፈተና ትኾናለች ተብላ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል፤ ባለ ብዙ ልምዷ ሲፈን ሀሰንም በውድድሩ ለሜዳሊያ ከሚጠበቁት አትሌቶች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ያም ኾኖ ግን ኢትዮጵያን የወከሉት ጉዳፍ ፀጋየ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና መዲና ኢሳ ለሀገራቸው የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ድል ለኢትዮጵያውያንⵑ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here