የኦሎምፒክ ድምቀት!

0
297

ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1956 ነው። ይኽውም በአውስትራሊያ ሜልቦርን በተደረገው 16ኛው ኦሎምፒክ መኾኑ ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ኢትዮጵያ በተለይ በአትሌቲክስ ዓለምን ያስደነቁ ሯጮችን አፍርታለች። በእነዚህ አትሌቶቿም ኢትዮጵያ የኦሎምፒኩ ድምቀት ኾና ቀጥላለች።

በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ አበበ ቢቂላ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ሀይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጌጤ ዋሜ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር እና ሌሎች በትውልድ ቅበብሎሽ ውስጥ ኢትዮጵያን እያስጠሩ ቀጥለዋል። በመኾኑም “ኦሎምፒክ”ሲነሳ የኢትዮጵያ ስም መታዎቂያ እስከ መኾን ደርሷል።

ኢትዮጵያ ከሜልቦርን ኦሎምፒክ በስተቀር በተሳተፈችባቸው ውድድሮች ሁሉ ሜዳሊያ ሳታገኝ የቀረችበት አጋጣሚ የለም። በመኾኑም ኦሎምፒክ ሲባል ምንጊዜም ኢትዮጵያ ትጠበቃለች። ያለ ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ምንም ነው የሚሉ በርካቶች ኾነዋል። ይህም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ብቻ ሳይኾን “ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር እነ አበበ ቢቀላን እና ሌሎችን እያነሱ ተሳትፎዋን እና ተጠባቂነቷን በየጊዜው ይዘግባሉ።

በኢትዮጵያውያን የተመዘገቡ አንዳንድ ሜዳሊያዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካም የመጀመሪያ በመኾናቸው በታሪክ ተመዝግበዋል። አበበ ቢቂላ፣ ደራርቱ ቱሉ እና ፋጡማ ሮባ በኦሎምፒክ ያስመዘገቡት ፋና ወጊ ድል በአፍሪካ የመጀመሪያ መኾኑን ልብ ይሏል። ኢትዮጵያ እስካሁንም 23 ወርቅ፣ 12 የብር እና 23 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት የ58 የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎች ባለቤትም ናት።

በኦሎምፒክ ውድድሮች ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ በአፍሪካ ከፍተኛ ሜዳሊያ በማግኘት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ ከተሳትፎ ባለፈ በተለይም ደግሞ በረጅም ርቀት ሩጫዎች እንድትጠበቅ ኾኗል። ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው በ33ኛው የፓሪስ የኦሎምፒክም ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ውድድሮች በተጨማሪ በሌሎችም ዘርፎችም ምርጥ ስፖርተኞቿን ይዛ እየተወዳደረች ትገኛለች።

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በሬዲዮ ፋና፣ በኢቢሲ እንዲሁም በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በስፖርት ጋዜጠኝነት የሠራው እና አሁንም የኢትዮጵያን ስፖርት በቅርበት የሚከታተለው ታምሩ ዓለሙ ኢትዮጵያውያን በፓሪስ ኦሎምፒክ ለድል የሚበቁባቸውን ምክንያቶች እና ሊያርሟቸው የሚገባቸውን ክፍተቶች አብራርቷል።

ታምሩ እንዳለውም ኢትዮጵያ በ5 ሺህ፣ በ10 ሺህ እና በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ3 ሺህ መሰናክል ወንዶች ከሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪዎች የእኛ አትሌቶቹ በሁሉም መመዘኛ “በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ስለሚገኙ ውጤት መጠበቅ ተገቢ ነው”። ጋዜጠኛው ሲቀጥል እንዳብራራው ጉዳፍ፣ ሐጎስ፣ ቀነኒሳ፣ አማኒ፣ ትዕግስት አሰፋ እና ለሜቻ ካላቸው ወቅታዊ ብቃት እና ልምድ የተነሳ ሜዳሊያ ውስጥ ይገባሉም ነው ያለው።

ቀነኒሳም ካለው ልምድ እና ብልጠት አንጻር በማራቶን ውድድር ለውጤት መታጨቱ ጋዜጠኛው ተገቢ ነው ይላል። “ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ መሰናክል ጥሩ ሰዓት አለው። 5 ሺህ ሜትርን ጨምሮ በእነዚህ ውድድሮች ተስፋ ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ” ብሏል ታምሩ። ታምሩ ፅጌ ዱጉማን በ800 ሜትር እና ብርቄ ኃየሎምን በ1 ሺህ 5 መቶ ሜትር ወርቅ እንጠብቃለን ነው ያለው።

ነገር ግን በተስፋ ውስጥ የሚስተዋሉ ሰጋቶች እንዳሉም ጠቁሟል። ይኽውም ዘንድሮ ጥሩ ቡድናዊ ሥራ ቢስተዋልም የብልጠት እና የአጨራረስ ክፍተቱን ይታያሉ። ባለሙያዎች እግር በግር እየተከታተሉ ማረም ይገባል የሚል ምክር ይሰጣል። በተደረጉ የተለያዩ ርቀቶች አትሌቶቻችን አንደኛ ያልወጡት በአቅም ማጣት ሳይኾን በብልጠት ውስንነት ነው። ይህን ችግር ከተስተካከለ ብዙ የወርቅ ሜዳሊያ ሊመዘገብ እንደሚችል ታምሩ አብራርቷል።

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ መሠረት መንግስቴ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከሩጫ በተጨማሪም በርምጃ በወንዶች የ20 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ምስጋናው ዋቁማ ርቀቱን በ 1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ በኾነ ሰዓት በስድስተኝነት አጠናቋል። ይህም በኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛው እንደኾነ ተናግሯል።

በሴቶች ውኃ ዋና ጥሩ ተስፋ ታይቷል ነው ያሉት። በእነዚህ መስኮችም በቁርጠኝነት ከተሠራ በቀጣይ ውድድሮች የተሻለ ወጤት ማስመዝገብ ይቻላል ነው ያሉት። መምህር መሠረት ጨምረው እንዳሉት በወንዶች 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ርቀት ጠንካራ ልጆች ቢኖሩንም ከሌሎች ሀገራት አትሌቶችም ጠንካራ ፉክክር ይጠበቃል ብለዋል። ስለዚህም “ለማሸነፍ አቅሙ አለን፤ ብልጠት ላይ ግን ሊታሰብበት ይገባል” ሲሉ መክረዋል።

አትሌቶች በመደዳ እየኾኑ ጉልበታቸውን ከማድከም ተቆጥበው በሩጦ-አስሩጦ የማድከም ጥበብ ውስጥ መድከም ያለበት አንድ አትሌት ብቻ ነው። ሌላው በዚህ ወቅት ትንፋሽ እና ጉልበት መሠብሠብ ይገባዋል። በቃ! የተወዳዳሪዎችን ወቅታዊ ብቃት እና ክፍተትም አውቆ መዘጋጀት ለድል ያበቃል ብለዋል መምህሩ።

በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ በ32 ስፖርት አይነቶች ከ10 ሺህ 500 በላይ አትሌቶች እየተወዳደሩበት ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ትናንት በእነ አበበ፣ ምሩጽ፣ ደራርቱ፣ ሀይሌ፣ ቀነኒሳ፣ መሰረት፣ ጥሩነሽ እና ሌሎች የመድረኩ ድምቀት ነበረች። ዛሬም ለክብሯ ወርቅ እና ብር ፓሪስ ላይ ከከተሙ ልጆቿ እየጠበቀች ነው።

ድል ለኢትዮጵያውያን!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here