ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያየ ርቀት ለወርቅ ሜዳሊያ የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ያካተተው ሁለተኛው ዙር የኦሎምፒክ ልዑክ ፈረንሳይ ፓሪስ ገብቷል። ፓሪስ የገባው ሁለተኛው ዙር ልዑክ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ተወዳዳሪዎችን ያካተተ ነው፡፡
በልዑኩ ከተካተቱ አትሌቶች መካከል የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወት፣ ሰለሞን ባረጋ እና ፅጌ ዱጉማ ይገኙበታል፡፡ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር እና 1 ሺህ 500 ሜትር፣ በሴት 800 ሜትር እና 5 ሺህ ሜትር የሚወዳደሩ አትሌቶች ፓሪስ መግባታቸውን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
ልዑኩ ቻርልስ ደጎል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና በፈረንሳይ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አቀባበል አድርገውለታል፡፡
በጉጉት የሚጠበቀው እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኙበት የ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድርም በአትሌት ምሥጋና ዋቁማ ተሳታፊነት የፊታችን ሐሙስ ይካሄዳል፡፡ አርብ ደግሞ የ800 ሜትር እና 5 ሺህ ሴቶች፣ 1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያዎች ይደረጋሉ። በዕለቱ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር እንደሚካሄድ የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!