የማዕከላቱ ውጤት በተግባር!

0
167

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከ80 በመቶ በላይ የሚኾነው መልከዓ ምድሩ ለአትሌቲክስ ስፖርት የተመቼ እንደኾነ ይነገራል። የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አዲሱ ባይህ የአንድን ሀገር ስፖርት (የአትሌቲክስ) ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ ለመሄድ ታዳጊዎችን በአንድ ማዕከል ማሠባሠብ ተገቢ ነው የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

የማሠልጠኛ ግብዓት በማሟላት በባለሙያ ማሠልጠን ኹነኛ መፍትሔ እንደኾነ የሀገረ ኬንያን አትሌቲክስ የማሠልጠኛ ማዕከላት ያስገኙትን እምርታ ዋቢ አድርገው አብራርተዋል። በኬንያ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2021 “ፔቭ ዘ አትሌቲክስ ዌይ” በሚል ርዕስ በ60 ታዳጊ አትሌቶች ላይ የተሠራ ጥናት ያመጣውን ውጤት ማጣቀሻ አድርገዋል።

በጥናቱ 30 በግላቸው የሚሠሩ እና 30 ደግሞ በማዕከል ታቅፈው በዘመናዊ የማሠልጠኛ ቁሳቁስ እንዲሁም በባለሙያ እየተደገፉ የሚሠለጥኑ አትሌቶች ተካትተውበታል ብለዋል መምህሩ። በግላቸው የሚሠሩ ታዳጊዎች አንድም ልዩ ልዩ ዓለማዊ ነገሮች እያዘናጓቸው እንዲሁም የቤተሰብ የዕለት ተዕለት አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረባቸው አዘውትረው ልምምድ አይሠሩም። ቢሠሩም የግብዓት እና የባለሙያዎችን ክትትል፣ ድጋፍ እና እገዛ አያገኙም። በመኾኑም ለ60ዎቹ ታዳጊዎች በተዘጋጀው የፓይለት( ሙከራ) ውድድር በግላቸው ከሠሩት ታዳጊዎች መካከል አሸናፊ የኾኑት ሦሥቱ ብቻ ናቸው ይላሉ። ስፖርቱን ሥራቸው አድርገው የቀጠሉትም ሦሥቱ ብቻ መኾናቸውን መምህሩ ገልጸዋል።

በአንጻሩ በአትሌቲክስ መዕከል ታቅፈው ከሠለጠኑት 30 ታዳጊዎች መካከል 28ቱ ውጤታማ ኾነው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።ጉዳዩን ወደ አማራ ክልል ስናመጣው ከ80 በመቶ በላይ የሚኾነው መልከዓ ምድሩ ለአትሌቲክስ ስፖርት የተመቼ ነው አሉን አቶ አዲሱ። መንግሥት ታዳጊዎች በአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ቢሠለጥኑ ውጤታማ እንደሚኾኑ በመገንዘብ የአትሌቲክስ የማሠልጠኛ ማዕከላት በተመረጡ ቦታዎች እንዲገነቡ ከማቀድ ባለፈ ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል።

“ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ” ያምራልና ከሰሜን ሸዋ የተገኘችው አትሌት አበበች አፈወርቅ እንደምትለው ከደብረብርሃን የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ተነስታ አኹን በትልልቅ ውድድሮች እየተሳተፈች ነው። እርሷ እንደምትለው በማዕከል ታቅፋ እንድትሠለጥን ዕድሉን ማግኘቷ ለስኬት አብቅቷታል። በሚደረግላት ሙያዊ ድጋፍ እና በትጋቷ በብሔራዊ ቡድን ተመርጣ የሀገሯን መለያ ለብሳ በዓለም አደባባይ በ10ሺህ እና በግማሽ ማራቶን በኔዘርላንድ መወዳደር ችላለች።በጣሊያን፣ በኮሎምቢያ እና በስፔን ሀገራት በመወዳደር በርካታ አመርቂ ውጤቶችንም አስመዝግባለች።

አትሌቷ ስለውጤቷ ተጠይቃ በማዕከል ታቅፋ መሥራቷ ለውጤት እንዳበቃትም ነግራናለች። ከእርሷ ጋር ስፖርቱን ጀምረው ማሠልጠኛ ያልገቡ ልጆች ለውጤት እንዳልበቁ በመጠቆም። “ሰሜን ሸዋ ለአትሌቲክስ የተመቼ አካባቢ ነው ” የምትለው አበበች እንደ እርሷ ኹሉ ሌሎች ታዳጊዎችም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እና ለስኬት በቅተው የሀገር እና የወገን መኩሪያ ይኾኑ ዘንድ በማዕከል መሠልጠን ይገባቸዋል ብላለች።

በፖላንድ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊ የኾነችው አትሌት ቃልኪዳን ፈንቴም የደብረ ብርሃን ማዕከል ፍሬ ናት። አትሌት ቃልኪዳን በፖላንድ ለ16 ኛ ጊዜ በተካሄደው ውድድር አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች፤ የሀገሯን ሰንደቅ ዓላማም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጋለች::

በዱባይ ማራቶን የቦታውን ክብረ ወሰን ሰብሮ በአሸናፊነት ያጠናቀቀው አትሌት ጌታነህ ሞላም የዚሁ ማዕከል ውጤት ነው። ወሎ ተንታ የአትሌቲክስ የማሠልጠኛ ማዕከል ካፈራቸው አትሌቶች መካከል ፂዮን አበበ ተጠቃሽ ናት። አትሌቷ በ2015 ዓ.ም በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍ ውጤት ማምጣት የቻለች አትሌት ናት። ፂዮን እንዳለችው በማዕከል ገብታ ባትሰለጥን ኑሮ ለስኬት አትበቃም ነበር። “ይህ ማዕከል መኖሩ በየወረዳዎች የሚገኙ ወጣት አትሌቶችንም ከማነቃቃቱ ባሻገር የተሻሉ ኹነው እንዲወጡ ያደረገ ነውም” ብላለች።

የአትሌቲክስ የማሠልጠኛ ማዕከላቱ የዚህን ያህል ውጤታማ አትሌቶች የሚፈሩበት ከኾነ በጅምር ያሉትን ለማጠናቀቅ ምን ያህል ተሠርቷል? በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር ባንተዓምላክ ሙላት ክልሉ ከ2010 ዓ.ም በፊት የነበረው የማሠልጠኛ ማዕከል ደብረ ብርሃን ብቻ እንደነበር ያነሳሉ። ቀስበቀስ ግን መንግሥት ጥቅሙን በመገንዘብ ሌሎች የማሠልጠኛ ማዕከላት በተመረጡ ሥፍራዎች እንዲገነቡ መወሰኑ ለዘርፉ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያመላክታል ባይ ናቸው።

በቢሮው በዕቅድ ከተያዙት 16 የማሠልጠኛ ማዕከላት መካከልም የደብረ ብርሃን፣ ጉና፣ ተንታ እና ደጋ ዳሞትን አጠናቅቆ ወደ ሥራ በማስገባት በርካታ ለሀገር ውለታ ከፋይ የኾኑ አትሌቶች እንዲወጡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። የዳባት፣ቲሊሊ፣ደባርቅ እና ሰከላ ማዕከላት ግንባታቸው ከ80 በመቶ በላይ ማጠናቀቅ ተችሏል። እነዚህን ማዕከላት አስመርቆ ሠልጣኝ ልጆችን ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መልምሎ ለማስገባት ቢሮው ሲዘጋጅ የጸጥታው ችግር መላ ሂደቱን አስተጓጉሎታል ነው ያሉት። የደባርቅ ማዕከል ሳይመረቅም ቢኾን ሥራ መጀመሩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

“አንዳንዶቹ ታጥረው፣ መሠረታቸው ወጥቶ፣ የጠረጋ ሥራ ተከናውኖ በጅምር ሥራ ላይ እንዳሉ ክልሉ በተደጋጋሚ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ከአቅም በላይ በኾነ ሳንካ ቁመዋል” ነው ያሉት። ዳይሬክተሩ የክልሉ ጸጥታ ኹኔታ ሲስተካከል ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን ለማከናዎን እንቅስቃሴ ላይ ነን ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here