የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለአሸናፊዎች የሚሰጠውን የሽልማት መጠን አሳደገ።

0
416

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በኮትዲቯር እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከጥር 13/2024 እስከ የካቲት 11/2024 በሚደረገው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ለሚኾነው ብሔራዊ ቡድን የሚሰጠውን ሽልማት ወደ 40 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡

በውድድሩ ሻምፒዮን ለሚኾነው ሀገር ሰባት ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል፡፡ በሁለተኛነት ለሚያጠናቅቀው ብሔራዊ ቡድን አራት ሚሊዮን ዶላር እንደሚበረከትለት ተገልጿል፡፡

የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ሀገራትም 2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ዶላር እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡ አራቱ የሩብ ፍጻሜ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድኖችም አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ዶላር ተመድቦላቸዋል ነው የተባለው፡፡

የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ(ዶ.ር) የአሸናፊዎች ሽልማት ከቀድሞው የገንዘብ መጠን ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ካፍ እግር ኳስን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ዶክተር ሞቴሴፔ ከሽልማት ገንዘቡ የተወሰነው መጠን የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶችን ለማሳለጥ እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተጠቃሚ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸው የጸና መኾኑን ጠቁመዋል ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here