እውቁ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች አንዲ ሙሬይ ከፓሪስ ኦሎምፒክ በኋላ ራኬቱን ሊሰቅል ነው፡፡

0
206

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ተጫዋቾች ውስጥ ስኮትላንዳዊው አንዲ ሙሬይ አንዱ ነው፡፡ የ37 ዓመቱ አንዲ ሙሬይ በፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገሩን ወክሎ በነጠላ እና በጥምር የቴኒስ ውድድሮችን ካደረገ በኋላ ራኬት እንደሚሰቅል የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

”ፓሪስ የምሄደው የመጨረሻውን የቴኒስ ውድድሬን ለማድረግ ነው“ በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ያሰፈረው አንዲ ሙሬይ በዚህ ውድድር ታላቋን ብሪታኒያ ወክሎ የሚጫወተውም ለመጨረሻ ጊዜ መኾኑን አሳውቋል፡፡ አንዲ ሙሬይ በ2008 እ.ኤ.አ ቤጂንግ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ጣፋጭ ድሎችን አሳክቷል።

ሙሬይ በለንደን እና ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦሎምፒኮች ሁለት ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያን ያሸነፈ ብቸኛው የወንዶች ሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ተብሎም ስሙ በክብር ሰፍሯል፡፡ የሦስት ጊዜ ግራንድ ስላም አሸናፊው ሙሬይ ሁለት ጊዜ የዌምብልደን የሜዳ ቴኒስ አሸናፊ በመኾንም ስሙን ከነ ኖቫክ ጆኮቪች፣ ራፋኤል ናዳል እና ሮጀር ፌዴረር ተርታ ለማስጠራት ችሏል፡፡

በ2019 ጉዳት አጋጥሞት የቀዶ ጥገና ካደረገ በኋላ ግን በቀደመ አቋሙ ላይ መገኘት አልቻለም፡፡ “የሜዳ ቴኒስ ስፖርትን በጣም ብወደውም ከጉዳቴ በኋላ ብዙም ውጤታማ መኾን አልቻልኩም” ያለው ሙሬይ “ከፓሪስ ኦሎምፒክ በኋላ ራኬቴን ለመስቀል አስቤያለሁ“ በማለት አሳውቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here