ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር እና የሕዝብ ክብር በአደራ የያዙ ጀግኖች በቅንጡዋ ከተማ ይከትማሉ፡፡ በዚያች ከተማ ድል አድርጎ የሀገርን ሠንደቅ ከሁሉም ሠንደቆች አልቆ ማውለብለብ የሁሉም ሕልም ነው፡፡
ሕልማቸው የሚሳካላቸው ጀግኖች በጥረታቸው ያመጡትን ድል በሠንደቃቸው ከፍታ ይገልጹታል፡፡ ለሠንደቅ ፍቅር፣ ለሀገር እና ለሕዝብ ክብር ሲባል ላባቸውን ያፈስሳሉ፣ እስከመጨረሻው ድረስ አንገት ለአንገት ይተናነቃሉ፡፡ እንኳን ድግስ ደግሳ እንዲያውም የምትወደደዋ የፈረንሳይዋ መናገሻ ፓሪስ በሽርጉድ ከርማለች፡፡ ድግሱ አምሯል፡፡ ዓይኖች ሁሉ ወደ ፓሪስ ሊመለከቱ ቀናት ብቻ ቀርተዋል፡፡ ቅንጡዋ ከተማ ተናፋቂውን ውድድር ኦሎምፒክን አዘጋጅታለችና፡፡
የኦሎምፒክ ጨዋታ ታሪክ ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት እንደሚመዘዝ ይነገራል፡፡ በአውሮፓ ታሪክ በሥነ ጽሑፍ፣ በታሪክ፣ በኪነ ጥበብ፣ በፍልስፍና፣ በኪነ ሕንጻ እና በሌሎች ዘርፎች ቀዳሚውን ቦታ እንደምትይዝ የሚነገርላት ጥንታዊቷ ግሪክ ለዚህ ጨዋታ ጀማሪ እንደኾነች ይነገራል፡፡ ለዚህ ጨዋታ መነሻ እንደኾኑ የሚነገርላቸው ደግሞ የጥንታዊት ግሪክ የበዓላት ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ለሺህ ዓመታት የዘለቀው ይህ ከእሴት እና ከባሕል ጋር ተያይዞ የተነሳው ኦሎምፒክ ተወዳጅ ነው፡፡
የመጀመሪያው የኦሎምፒክ ታሪክ የጽሑፍ ማስረጃ እንደሚያመላክተው ኦሎምፒክ የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ776 ዓ.ዓ ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በየአራት ዓመቱ ይደረጉ የነበሩት ለግሪክ አምላክ “ለዜውስ” ክብር ሲባል ነበር፡፡ ከዚያ በመቀጠል ግን ሙዚቃ፣ ቲያትር፣ መዝሙር፣ ግጥም እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎች በኦሎምፒክ ይቀርቡ ጀመር፡፡
ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ ታላቅ ክብረ በዓል ሲደረግበት የኖረው ኦሎምፒክ ከክርስቶስ ልደት በኃላም ቀጠለ፡፡ ለጣኦታቶቻቸው ታላቅ ክብር የሚሰጡት ግሪካውያን ክብር ከሚገልጡበት በዓል ጋር ጥበብን በዚያው ይገልጣሉ፡፡ ዘመን ዘመንን እየተካ፣ ነገሥታቱ እያለፉ፣ ሌሎች እየተተኩ ቀጠለ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ393 ዓ.ም በሮም የነገሠው ቴዎዶስዮስ ከእርሱ ቀድመው እንደተነሱ ነገሥታት ሁሉ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች አልተደሰተም፡፡ ይልቅስ ኦሎምፒክን ያስቆም ዘንድ ወደደ፡፡ ቀዳማዊ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን በሃይማኖታዊ ምክንያቶች እንዳይደረጉ ሲል አገዳቸው፡፡ ይህም ኦሎምፒክ ሃይማኖትን ትቶ አረማዊነትን ያበረታታል በማለት ነበር እገዳውን ያስተላለፈው፡፡ የሮማው ንጉሥ ያስተላለፈው እገዳም እስከ ዘመናዊው ዘመን ድረስ አልተነሳም ነበር፡፡
ለዘመናት ታግዶ የነበረው የኦሎምፒክ ጨዋታ ከዘመናት በኋላ እ. አ. አ ከሰኔ 16 እስከ 23 ድረስ በ1894 ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጉባኤ ተነቃቃ፡፡ ሁለት ሺህ ታዳሚዎች በተገኙበት በዚህ ጉባኤ የኦሎምፒክ ስፖርት እንደገና ተነሳ፡፡ ሰኔ 23 ቀን ጉባኤው ሲጠናቀቅ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች እንደገና ተወለዱ ይላል ታሪክ፡፡ በዚሁ ቀን የኦሎምፒክ ኮሚቴም ተቋቋመ፡፡
የሰውን ልጅ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጥንካሬን ማሳደግ፣ የተሻለ ሰላም የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት በማሰብ በጋራ መግባባት እና ጓደኝነት መንፈስ ወጣቶችን በስፖርት ማስተማር፣ የኦሎምፒክ ሀሳቦችን ከመላው ዓለም ጋር መጋራት እና ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ስሜት መፍጠር፣ በየአራት ዓመቱ ለትልቁ የስፖርት በዓል ከመላው ዓለም የተውጣጡ ስፖርተኞችን በማሠባሠብ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ማድረግ በጉባኤው የተወሰኑ የኦሎምፒክ መርሆዎች ነበሩ፡፡
ከዚህ በኋላ በሮማው ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ተቋርጦ የነበረው የኦሎምፒክ ጨዋታ እ. አ. አ በ1896 ዓ.ም በሚያዚያ ወር በመነሻው ሀገር በግሪኳ መናገሻ አቴንስ ተካሄደ፡፡ ይሄም ዝግጅት የዘመናዊው የመጀመሪያው የኦሎምፒክ ጨዋታ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ በ1900 የተካሄደውን የኦሎምፒክ ጨዋታ ደግሞ የፈረንሳዩዋ የቱሪስቶች መናገሻ፣ የኤፈል ታወር መገኛ ከተማ ፓሪስ አዘጋጀች፡፡
በ1900 የፓሪስ ኦሎሚክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶችም ተሳታፊ ኾኑ፡፡ በዚህም ውድድር ከታላቋ ብሪታኒያ የሄደችው ቻርሎት ኩፐር በኦሎምፒክ ድል ያስመዘገበች የመጀመሪያዋ ሴት በመኾን ታሪክ ጻፈች፡፡ በዚህ ዘመን ከተሳተፉ 997 አትሌቶች መካከል 22 ሴቶች ነበሩ ይላል የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ፡፡ ከአቴንስ ቀጥላ ኦሎምፒክን ያስተናገደችው ፓሪስ የ2024ቱን የኦሎምፒክ ውድድርን አዘጋጅታለች፡፡
ፍራንስ 24 በዘገባው የብርሃን ከተማ ፓሪስ ከሐምሌ 19/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም ድረስ በዓለም ላይ ካሉት ምርጥ አትሌቶች ጋር ትሰነብታለች ብሏል፡፡ የመክፍቻ ዝግጅቱ ከስታዲዬም ውጭ በኤፊል ታወር ሥር ባሉ ያማሩ የፈንሳይ ጎዳናዎች ይካሄዳል፡፡ ከ6 ሺህ እስከ 7 ሺህ የሚደርሱ ብርቅዬ የዓለም አትሌቶች በሲን ወንዝ አቋርጠው ወደ ኤፍል ታወር ይጓዛሉ ይላል የፍራንስ 24 ዘገባ፡፡
ፓሪስ ከመክፈቻው እስከ ፍጻሜው ድረስ በብርቅዬ አትሌቶች፣ አሠልጣኞች እና በስፖርት ቤተሰቦች ከውበት በላይ ውበት ትጨምራለች፡፡ እጅግም ደምቃ ትታያለች፡፡ የዓለም ዓይኖች ሁሉ በአሻገር ይመለከቷታል፡፡ በዚያች ከተማ ከፍ የምትል የሀገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ በስስት የሚያዩም ብዙዎች ናቸው፡፡ በደስታ እንባ ታጅባ ከሁሉ ልቃ ከፍ የምትለው ሠንደቅ ታስከብራለችና፡፡ ያን የሚያደርጉ አትሌቶች ደግሞ ገናና ስማቸውን በታሪክ ላይ ያሰፍራሉ፡፡
ግማሽ ሚሊዮን የሚኾኑ ተመልካቾች ደግሞ በወንዙ ዳርቻ ኾነው ያን ውብ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ይመለከታሉ ነው የተባለው፡፡ በፖለቲካ የተለያዩ አመለካከቶች ውጥረት ውስጥ ያለችው ፈረንሳይን በዚህ ውድድር ከስፖርት የዘለለ ነጥብ ታስቆጥርበታለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዳር ዳር ኾነው ስሟን ለሚያባጥሏት ሰዎችም ያማረ ድግስ ደግሳ ስሟን ከፍ እንደምታደርግበት የብዙዎች ግምት ነው፡፡
የሀገራትን ስም እና ዝና ከፍ በማድረግ የሚታወቀው ኦሎምፒክ የፈረንሳይን እና የዋና ከተማዋን የፓሪስን ዝናም ከፍ እንደሚያደርግ ይገመታል፡፡ ለመክፈቻው ሥነ ሥርዓት የሚቀርቡ የሙዚቃ ድግሶች እና ሌሎች ሥነ ሥርዓቶች ታላቅ ዝግጅት የተደረገባቸው ናቸው ተብሏል፡፡ በፈረንሳይ ውስጥ አሉ የሚባሉ የዘርፉ ሰዎች የተካተቱበት እንደኾነም ተመላክቷል፡፡ በሙዚቃ ድግሱ እና በሌሎች የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የታሪክ ምሁራን ሁሉ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
በ12 ክፍሎች እንደተከፋፈለ የተነገረው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ 3 ሺህ የሚደርሱ ዳንሰኞች እና ዘፋኞች ይሳተፉበታል፡፡ በወንዞች፣ በድልድዮች እና በሐውልቱ ላይ ይደምቃሉ፡፡ ታላቁ የኖተርዳም ካቴዴራል ክብር እንደተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡ ወግ አጥባቂ ፈረንሳውያንን ባያስደስትም የኦሎምፒክ ድግሱ በዓለም ዙሪያ የባሕል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የጾታ ብዝኃነት በዓል እንደሚኾን ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!