ኤንዞ ፈርናንዴዝ እና በቼልሲ ያመጣው ጣጣ

0
261

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ስኬታማ ጊዜን ያላሳለፈው የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ ለአዲሱ አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካም አዲስ ፈተና ተጋርጦባቸዋል፡፡

ሌስተር ሲቲን ከእንግሊዝ የታችኛው ዲቪዚዮን በዓመቱ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመለሱት ኤንዞ ማሬስካ በቼልሲ ቤትም ሰማያዊዎቹን ይበልጥ ያደምቃሉ ተብለው ተጠብቀዋል፡፡ ቼልሲ ከሩሲያው ባለሀብት ሮማን አብራሞቪች ወደ አሜሪካዊው ባለ ሀብት ቶድ ቦሊ ከተሸጋገረ በኋላ በቀደመ ውጤታማነቱ አልቀጠለም፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚነሳው የቼልሲዉ ቱጃር “ሀብት” እንጂ የእግር ኳስ ዕውቀት ሳይኖራቸው ክለቡን ለመምራት የፈለጉበት መንገድ ነው ተብሏል፡፡

የቼልሲው ባለ ሀብት በተጨዋቾች ዝውውር እጃቸውን ከማስገባታቸው በቀር ለተጨዋቾች ዝውውር እጃቸው እንደማይሰስት ግን በሰማያዊዎቹ ቤት ያሉት ድንቅ ተጨዋቾች እማኝ ናቸው፡፡ ኮል ፓልመር፣ ኤንዞ ፈርናንዴዝ፣ ኒኮላስ ጃክሰን፣ ሮበርት ሳንቼዝ፣ አክሴል ዲሳሲ፣ ማርክ ኩኩሬላ፣ ቤኖይት ባዲያሽሊ፣ ዌስሊ ፎፋና፣ ካርኔ ቹኩሜካ፣ ሞይሰስ ካይሲዶ፣ ሚካይሎ ሙድሪክ፣ ኖኑ ማዱኬ፣ ክርስቶፈር ንኩንኩ እና ሌሎችም ምዕራብ ለንደንን ደማቅ ሰማያዊ ለማድረግ በቅርብ ዓመታት ብዙ ገንዘብ የወጣባቸው ተጨዋቾች ናቸው፡፡

ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ እነዚህን እና ሌሎችንም ድንቅ የእግር ኳስ ባለ ክህሎቶች ይመሩ ዘንድ የተሰጣቸውን ዕድል በውጤት አላጀቡትም፡፡ የቼልሲ የቡድን ጥልቀት ብቻ ሳይኾን የቡድን ጥራትም በፖቺቲኖ የአሠልጣኝነት ዘመን መክኗል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ከቼልሲ የተሰናበቱትን ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ተክተው በምዕራብ ለንደን የተገኙት ኤንዞ ማሬስካ የቼልሲን መልበሻ ክፍል በአግባቡ መቆጣጠር ቀዳሚ ሥራቸው ይኾናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአዲስ ቼልሲን የሚቀላቀሉ ተጨዋቾችን ከክለቡ ጋር ማዋሃድ እና በተጨዋቾቹ ዘንድ የአሸናፊነትን ሥነ ልቦና ማስረጽ ደግሞ የማሬስካ ቀጣይ የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡ አርጀንቲናዊው ኤንዞ ፈርናንዴዝ ቼልሲን በውድ ዋጋ ከተቀላቀሉት ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ፈርናንዴዝ ከክለቡ ቼልሲ ጋር ውጤታማ ጊዜን ማሳለፍ ባይችልም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሁለት ትላልቅ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

አርጀንቲና በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ስትኾን እና በቅርቡ በአሜሪካ በተደረገው የኮፓ አሜሪካ ጨዋታ ዋንጫ ስታነሳ ኤንዞ ፈርናንዴዝ የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋች ነው፡፡ አርጀንቲና በዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ ያሸነፈችው ፈረንሳይን መኾኑ ይታወሳል፤ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ በሚመዘዝ ጥቁር ተጨዋቾች የተዋቀረ መኾኑም የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

ኤንዞ ፈርናንዴዝ በቅርቡ ሀገሩ የኮፓ አሜሪካን ዋንጫ ማሸነፏን ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በአውቶቡስ ውስጥ ኾነው እየዘፈኑ ደስታቸውን የገለጹበትን ቪዲዮ ለዓለም አጋርቷል፡፡ አርጀንቲናዊያን ደስታቸውን በዘፈን መግለጻቸው እምብዛም አያስገርምም፤ ችግሩ የዘፈናቸው ግጥሞች የፈረንሳይ ተጨዋቾችን ከአፍሪካ መጤነት እና የቆዳ ቀለማቸውም ጥቁር መኾኑን መግለጻቸው ነው፡፡

በጥቁር ተጨዋቾች ላይ መልኩን እየቀያየረ የሚንጸባረቀው የዘረኝነት ትችት አሁን ደግሞ ተራው ለፈረንሳዊያን ጥቁር ተጨዋቾች ኾኗል፡፡ ኤንዞ ፈርናንዴዝ የቡድን አባላቱ በዓለም ዋንጫው የዋንጫ ተፎካካሪያቸው የነበሩትን ፈረንሳዊያን ለማብሸቅ ሲሉ ዘረኝነትን ማንጸባረቃቸው በብዙዎች ዘንድ እያስወቀሳቸው ይገኛል፡፡

በተለይ ቪዲዮውን በማኅበራዊ ገጹ ያጋራው ኤንዞ ፈርናንዴዝ በብዙ ፈረንሳዊያን የቼልሲ ተጨዋቾች ዘንድ ነቀፌታን አስነስቶበታል፡፡ በማኅበራዊ ገጽ ከእሱ ጋር የነበራቸውን ትሥሥር ወዲያውኑ ያቋረጡ ፈረንሳዊያን ተጨዋቾችም እንዳሉ የቢቢሲ እና ስካይ ስፖርት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኤንዞ ፈርናንዴዝ ለድርጊቱ ይቅርታ መጠየቁን እና ዘረኝነት የሱ ሰብዕና እንዳልኾነ ደጋግሞ ገልጿል፤ የሚሰማው ባያገኝም፡፡

የዓለም እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ (ፊፋ)፣ የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌዴሬሽኖችም በጉዳዩ ላይ በጥልቀት እየመከሩ ስለመኾናቸው መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ የቼልሲ እግር ኳስ ክለብም ጉዳዩን ካጣራሁ በኋላ በፈርናንዴዝ ላይ ተገቢውን እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡

የቼልሲ አዲሱ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ አሁን ላይ ከቡድናቸው ጋር የቅድመ ዝግጅት ልምምድ እያደረጉ ይገኛሉ፤ በኮፓ አሜሪካው ጨዋታ ምክንያት እረፍት የተሰጠው ፈርናንዴዝም በቅርቡ ክለቡን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአሠልጣኙ ፈተና ይኾናል የተባለው ፈረንሳዊያን ጥቁር ተጨዋቾችን በዘረኝነት ከሰደባቸው ኤንዞ ፈርናንዴዝ ጋር እንዴት አግባብተው ክለባቸውን በኃላፊነት ይመራሉ? የሚለው ነው፡፡ በቼልሲ ቤት ሮበርት ሳንቼዝ፣ አክሴል ዲሳሲ፣ ቤኖይት ባዲያሽሊ፣ ዌስሊ ፎፋና እና ክርስቶፈር ንኩንኩ ፈረንሳዊያን ጥቁር ተጨዋቾች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here