ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ እና ኔዘርላንድን ለግማሽ ፍጻሜ አድርሷል። ዛሬ እና ነገ በሚከናወኑ ጨዋታዎች ደግሞ ለዋንጫ የሚደርሱ ቡድኖች ይለያሉ።
ዛሬ ፈረንሳይ እና ስፔን የሚያደርጉት ጨዋታም በጉጉት ይጠበቃል። ስፔን በውድድሩ በማራኪ ጨዋታ የጀርመኑ ድግስ ድምቀት ኾናለች። ታዳጊዎቹ ያማል እና ዊሊያምስ ለስፔን ውጤታማነት ትልቅ ድርሻን እየተወጡ ነው። በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አዘጋጅ እና ጠንካራዋ ጀርመንን ማሸነፏም የስፔንን አስፈሪነት ይበልጥ አሳይቷል። በውውድድሩ አስካሁን ያስቆጠረችው 11 ግብም ከየተትኛውም ቡድን የበለጠ ነው።
በአንጻሩ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን መልካሙ ነገር ለግማሽ ፍጻሜ መቅረቡ ብቻ ነው። ወደ ውድድሩ ሲመጣ የተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚያሳይ የተጠበቀው የዲዴር ዴሾ ቡድን በተገመተው ልክ አልተገኘም። ቡድኑ ለእይታ የማይመች እና በጎል ድርቅ የተመታ ጉዞን እያደረገ ነው። እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታቸው ቡድኑ በራሱ ተጫዋች ያስቆጠረው ግብ አንድ ብቻ ነው። እሷም የተገኘችው በፍጹም ቅጣት ምት መኾኗ የፈረንሳይን የማጥቃት ድክመት በግልጽ የሚያሳይ ኾኗል። ቀሪ ሁለት ግቦች በራስ ላይ የተቆጠሩ ናቸው።
በስፔን ብሔራዊ ቡድን በኩል ከጀርመን ጋር በነበረው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ዳኒ ካርቫሃል ጨዋታው ያመልጠዋል። አማካዩ ፔድሪ ደግሞ በጉዳት ምክኒያት ተሰላፊ አይኾንም። አጥቂዎቹ ያማል እና ዊልያምስ በስፔን በኩል ተጠባቂ ተጫዋቾች ናቸው። ተከላካዩ ኩኩሪያም በአውሮፓ ዋንጫው ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ ነው። ዛሬም የፈረንሳይ አጥቂዎችን በመግታት በኩል የሚኖረው ድርሻ ይጠበቃል።
በፈረንሳይ በኩል በቅጣትም ይሁን ጉዳት ለዛሬው ግጥሚያ ዝግጁ ያልኾነ ተጫዋች የለም። አጥቂዎቹ ኪሊያን ምባፔ እና አንቶን ግሪዝማን ጎሎችን እያስቆጠሩ አይደለም። በዛሬው ጨዋታ ጎል ወደ ማስቆጠር ካልተመለሱም ፈረንሳይ በጨዋታው ትቸገራለች። በማጥቃት ደካማ የተባለው የዴሾው ቡድን በመከላከል ግን ጠንካራ ነው። ለዚህም የተከላካዮች እና የአማካዩ ጥንካሬ በበጎ ይነሳል። በዚህ ጨዋታም “የአይደክሜው” ንጎሎ ካንቴ ብቃት ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በትልቅ ውድድር ከዚህ በፊት አምስት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፈረንሳይ ሦስት ጊዜ አሸንፋለች። አንዱ በስፔን የበላይነት ቀሪው ደግሞ አቻ መጠናቀቁን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያሳያል።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ሰዓት በባየርሙኒኩ አልያንዝ አሬና ስታዲየም ይካሄዳል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!