የተስፈኛው መዳረሻ እስከምን ድረስ ይኾን?

0
338

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ስፔናዊው ላሚን ያማል ገና በ16 ዓመቱ የእግር ኳስ ክህሎቱን በትልቁ የአውሮፓ ዋንጫ ላይ በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡

የባርሴሎናው የላሜሲያ አካዳሚ ፍሬ የኾነው ያማል፣ በቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች እና አሠልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝ የመሰለፍ ዕድል የተሰጠው በ15 ዓመት ከ10 ወር ዕድሜው ነው፡፡ በባርሴሎና የክለብ ታሪክ በትንሽ ዕድሜው የተጫወተ የሚል ክብርን የተጎናጸፈው ተስፈኛው ያማል የመጀመሪያ የነጥብ የክለቦች ጨዋታውን ያደረገው ባርሴሎና ሪያል ቤቲስን 4 ለ 0 በረታበት ጨዋታ የ 8 ደቂቃ የመሰለፍ ዕድልን በማግኘት ነው፡፡

ያማል ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር ወደ ጀርመን ተጉዞ ስፔን ክሮሺያን ባሸነፈችበት የመጀመሪያ ጨዋታ በ16 ዓመት ከሁለት ወሩ ለሀገሩ በመሰለፍ በትንሽ ዕድሜ የመሰለፍን ክብረ ወሰን ጨብጧል፡፡ የያማል የክለብ አጋሩ ስፔናዊው ጋቪ በ17 ዓመት ከሁለት ወሩ ለብሔራዊ ቡድኑ በመሰለፍ እና ግብ በማስቆጠር የክብረ ወሰኑ ባለቤት እንደነበር የስካይ ስፖርት መረጃ ያስረዳል፡፡

ያማል ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ባርሴሎና ከግራናዳ ጋር 2 አቻ በወጡበት ጨዋታ ግብ በማስቆጠርም የላሊጋው ባለ ትንሽ ዕድሜ ግብ አስቆጣሪ ኾኗል፡፡ በ16 ዓመቱ በአውሮፓ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ ፖላንዳዊው ካስፐር ኮዝሎውስኪ ይዞት የነበረውን ክብረ ወሰን በወራት ያሻሻለው ያማል ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ከፈረንሳይ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያም ተጠባቂው ተጫዋች ነው፡፡

በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2007 በስፔን የተወለደው ያማል አባቱ ሞሮኳዊ ሲኾኑ እናቱ ደግሞ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ናቸው፡፡ ያማል ከባርሴሎና ጋር እስከ 2026 የሚያቆይ ኮንትራት ቢኖረውም ዕድሜው 18 ዓመት ሲሞላ ካታሎናዊያኑ የልጁን ውል እስከ 2030 ለማራዘም ፍላጎት አላቸው፡፡

አሁን ላይ በዓለም እግር ኳስ ውድ ከሚባሉት ተጫዋቾች ተርታ የተሰለፈው ወጣቱ ያማል በብዙ የአውሮፓ ክለቦች የሚፈለግ ተጫዋችም መኾን ችሏል፡፡ የፈረንሳዩ ፓሪሰን ዠርማ በውድ ዋጋ ያማልን ከባርሴሎና ለማስኮብለል ከሚፈልጉት ክለቦች ውስጥ ስሙ በቀዳሚነት እየተነሳ ነው፡፡ በስፔኑ ላሊጋ በርካታ የዕድሜ ክብረ ወሰኖችን ያሻሻለው ያማል በግዙፉ የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታም ክብረ ወሰኖችን ማሻሻሉን ቀጥሏል፡፡

ዛሬ ምሽት በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ከኪሊያን ምባፔዋ ፈረንሳይ ጋር በግማሽ ፍጻሜው ሀገሩን ስፔንን ወክሎ የሚፋለመው ያማል ግብ የሚያስቆጥር ከኾነ የሌላ አዲስ ክብረ ወሰን ባለቤትም ይኾናል፡፡ ስፔን ለግማሽ ፍጻሜው እስከምትደርስ ድረስ በሁሉም ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል የተሰጠው ወጣቱ ተስፈኛ ለቡድን አጋሮቹ ሦስት ግብ የኾኑ ኳሶችን በማቀበል በአውሮፓ ዋንጫው ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡

መቶ በመቶ ጨዋታዎችን እያሸነፈች ለግማሽ ፍጻሜው የቀረበችው ስፔን በግራ መስመር ላሚን ያማል እና በቀኝ መስመር ደግሞ ኒኮ ዊሊያምስ የፈረንሳይን የተከላካይ መስመር ይፈትኑታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስካሁን በአውሮፓ ዋንጫው አንድ ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ብቻ ያስቆጠረው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አምበል እና አጥቂው ኪሊያን ምባፔ ዛሬም በእጅጉ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here