ባሕር ዳር: ሐምሌ01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ፣ የሪያል ማድሪድ እና የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሩድ ቫንስትሮይ ለማንቸስተር ዩናይትድ ረዳት አሠልጣኝ ለመኾን ተስማምቷል፡፡ እንግሊዛዊ ቢሊኔር ሰር ጂም ራትክሊፍ ኦልድትራፎርድ ከደረሱ በኋላ በማንቸስተር ዩናይትድ በርካታ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ሰር ጂም ራትክሊፍ በማንቸስተር ዩናይትድ የሃብት ድርሻ እንደገዙ የመጀመሪያው ዓላማቸው ክለቡን ወደ ቀደመ ኃያልነቱ እና ዝናው መመለስ እንደኾ ተናግረው ነበር፡፡ ታላቁን ክለብ ወደ ቀደም ዝናው እና ክብሩ ለመመለስ ደግሞ በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸው ይታወሳል።
ኔዘርላንዳዊውን አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን በአሠልጣኝነት መንበራቸው እንዲቀጥሉ የፈቀዱት ሰር ጂም ራትክሊፍ በአሠልጣኙ እና በክለቡ የታመነባቸውን የቡድን አባላት፣ ተጫዋቾች እና ሌሎችን ለማሟላት ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው፡፡ በአሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ የተወደደው እና የማንቸስተርን ቤት የሚያውቀው የቀድሞው ኮኮብ ሩድ ቫንስትሮይ ረዳት አሠልጣኝ እንዲሆን ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተው በመጨረሻም ተሳክቷል፡፡
ማንቸስተር ኢቪንግ ሩድ ቫንስትሮይ የማንስቸስተር ዩናይትድ ረዳት አሠልጣኝ ለመኾን መስማመቱን ጽፏል፡፡ “የቀድሞው የማንስቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሩድ ቫንስትሮይ በአዲስ ሚና ወደ ኦልድ ትራፎርድ ተመልሷል” ነው ያለው፡፡ ቫንስትሮይ ሌሎች ጥያቄዎች ቢቀርቡለትም የማንቸስተር ዩናይትድን ጥያቄ ተቀብሏል፡፡ በቅርቡ ከአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ጋር ለመተዋወቅ ዝግጁ ነው ተብሏል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2001 ኦልድትራፎርድ የደረሰው ሩድ ቫንስትሮይ በኦልድትራፎርድ ታሪክ የማይረሳቸው ድንቅ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ ድንቁ አጥቂ በማንቸስተር ዪናይትድ ያስቆጠራቸው ግቦች በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ ኔዘርላንዳዊ አጥቂ ሩድ ቫንስትሮይ በማንቸሰተር ዩናይትድ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት 100 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በኔዘርላንድ ክለቦች ጎምርቶ የእንግሊዙን ኃያል ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድን የተቀላቀለው ሩድ ቫንስትሮይ ከኔዘርላንዱ ሄርኔቨን ወደ ሌላኛው የኔዘርላንድ ክለብ ፒኤስቪ ኢንዶቨን በ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ፓውንድ ሲዘዋወር በወቅቱ የሀገሪቱ ክብረ ወሰን ኾኖ ተመዝግቦለት ነበር፡፡ በሁለት ዓመታት ቆይታው ለፒኤስቪ ኢንዶቨን 60 ግቦችን ያስቆጠረው ግብ አዳኙ ቫንስትሮይ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ቀልብ ሳበ፡፡
የቀድሞው የማንቸስተር አለቃ ሰር አሌክሰ ፈርጉሰንም አጥቂውን ተመለከቱት፡፡ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዕይታ ውስጥ የገባው ቫንስትሮይ በአውሮፓውያኑ ሚሊኒዬም ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊያደርገው የነበረው ዝውውር በጤና ምርምራ እከል ምክንያት ሳይሳካ ቀረ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም በ2001 የጤና ምርመራውን አልፎ በ19 ሚሊዮን ፓውንድ ኦልድትራሮርድ ደረሰ፡፡ ቫንስትሮይ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን አሠልጣኝነት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ዋንጫዎችን ከፍ አደረገ፡፡
በማንቸስተር ዩናይትድ አስደናቂ ጊዜያትን ያሳለፈው ቫንስትሮይ በ2006 ደግሞ ኃያሉን ክለብ ሪያል ማድሪድን ተቀላቀለ፡፡ በ2012 በ35 ዓመቱ ከእግር ኳስ ተጨዋችነት ራሱን ያገለለው ቫንስትሮይ ወደ ቀድሞ ክለቡ ፒኤስ ቪ ኢንዶቨን ተመልሶ በአሠልጣኝነት አገልግሏል፡፡ በሀገሩ ኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድንም በረዳት አሠልጣኝነት ሠርቷል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ኦልድትራፎርድ ተጉዞ የኤሪክ ቴን ሃንግ ረዳት አሠልጣኝ ለመኾን ተስማምቷል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ ኔርላንዳውያውያንን ተጨዋቾች ማቲየስ ዲላይት እና ጆሺዋ ዚርከዚን ለማስፈረም ጥረት ላይ እንደሚገኝም መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!