መምህሩ ወይስ ደቀ መዝሙሩ?

0
299

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁን ኮኮብ ከታናሹ ኮኮብ የሚያገናኘው የጨዋታ ቀን ደርሷል፡፡ አንደኛው ኮኮብ የሚያዝንበት፣ ሌላኛው ኮኮብ ደግሞ የሚቦርቅበት ምሽት ዛሬ ነው፡፡ ሁለቱም ሀገራቸውን በአምበልነት እየመሩ ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡ ከሀገራቸው ይልቅ የኮከቦቹ ትንቅንቅ የዘገባ ርዕስ ኾኗል፡፡

ታላቁ ኮኮብ ይህ ጨዋታ በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ የመጨረሻው ሊኾን ይችላል፡፡ ታናሹ ኮኮብ ግን ተደጋጋሚ እድሎች አሉት፡፡ የጀርመኑ አውሮፓ ዋንጫ ዛሬ ከብርቆቹ መካከል አንደኛውን በሀዘን ወደ ሀገሩ ይሸኛል። ሌላኛውን ደግሞ በደስታ አጅቦ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋል፡፡ የክርስቲያኖ ሮናልዶዋ ሀገር ፖርቱጋል እና የኪሊያን ምባፔዋ ሀገር ፈረንሳይ በሩብ ፍጻሜው ጨዋታ ተገናኝተዋል፡፡ ከሀገራቱ ጨዋታ ይልቅ ሁለቱ ከዋክብት በተቃራኒነት የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል፡፡ ከጀገነበት የእግር ኳስ ሜዳ ሊሰናበት ጥቂት ጊዜያት የሚቀሩት ባለ ብዙ ክብሩ እና ባለ ብዙ ዝናው ሮናልዶ፣ እርሱን እያየ ካደገው፣ አርዓያው አድርጎት ከኖረው እና በትኩስ ጉልበት ላይ ከሚገኘው ምባፔ ጋር ይፋለማል፡፡

ፖርቱጋላውያን ከውድ ልጃቸው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ ዓይናቸውን ጥለዋል፤ ፈረንሳውያንም ከኮከባቸው ኪሊያን ምባፔ ላይ ዓይናቸውን አያነሱም፡፡ የማዴራው ጀግና በፖርቱጋል መለያ ለፖርቱጋላውያን አስደናቂ የደስታ ጊዜያትን ሲሰጣቸው ኖረዋል፡፡ በእርግጥ የእርሱ የደስታ ስጦታ ለፖርቱጋላውያን ብቻ አይደለም፤ ከዓለም ዳር እስከ ዳር ለሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ጭምር እንጂ። ፖርቱጋላውያን በተከዙበት እና የሽንፈት መልእክተኛ በራቸውን በቆረቆረ ጊዜ ሁሉ እየደረሰ ለድል ሲያበቃቸው የኖረው ልጃቸው ዛሬም ደስታን እንደሚሰጣቸው ይጠብቃሉ፡፡ በታሪክ ካሳያቸው አይረሴ ጊዜ እና አስደናቂ ብቃት አንጻር ዛሬም ከእርሱ ብዙ ነገርን ይጠብቃሉ፡፡

ፈረንሳውያን ደግሞ በልጅነት እድሜው የዓለም ዋንጫን ለክብራቸው ካበረከተላቸው፣ በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ በአስደናቂ የእግር ኳስ ብቃት ሀገሩን ከፍ ከፍ ካደረገላቸው ከኪሊያን ምባፔ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፡፡ በ2016 የአውሮፓ ዋንጫን የነጠቃቻቸውን የክርስቲያኖ ሮናልዶዋን ሀገር ፖርቱጋልን ድል አድርጎ ጣፋጭ በቀል እንዲበቀልላቸው ይሻሉ፡፡

ከወደ ፖርቱጋል ያሉ ደጋፊዎች ደግሞ ሁልጊዜም ድል የሚርበው እና የማይዝለው ልጃቸው ዳግም ድል ነስቶ ደስታቸውን ከፍ እንደሚያደርግላቸው ይጠብቃሉ፡፡ ደስታ ወደ ሮናልዶ እና ፖርቱጋል ወይስ ወደ ምባፔ እና ፈረንሳይ ትሻገራለች፡፡ ሀዘንም እንዲሁ ወደ አንደኛው መሻገራቸው አይቀርም፡፡

ከለጋ እድሜው ጀምሮ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ሲያደንቀው ያደገው ኪሊያን ምባፔ ከጨዋታው አስቀድሞ በሰጠው አስተያየት ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር መጫወት ክብር ነው ብሏል፡፡ ምባፔ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በጀገነበት እና አራት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ወዳነሰባት ክለብ ሪያል ማድሪድ መዛወሩን ያስታወሰው ቢቢሲ ከአምስት ጊዜ የባለንዶር አሸናፊው ጋር መጫወት ደስታን ይፈጥራል ማለቱን ዘግቧል፡፡

ክርስቲያኖን ሲያደንቀው እንደኖረ የሚናገረው ምባፔ በጊዜ ሂደት ከእርሱ ጋር ለመገናኘት እና ብዙ ለመናጋገር እድል አግኝቻለሁ፤ አሁንም እንገናኛለን ብሏል፡፡ ምባፔ የሮናልዶዋን ሀገር ፖርቱጋልን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜው እንደሚደርሱ ያለውን ተስፋም ተናግሯል፡፡

ቢሶከር በዘገባው ፈረንሳይ እና ፖርቱጋል በሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረቱ ከሁለቱ ከዋክብት ላይ ነው ይላል፡፡ ሁለቱን ተጠባቂ ሀገራትን የሚያገናኘው የምሽቱ የሐምቡርግ ጨዋታ አንደኛውን አሰናብቶ አንደኛውን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ይሸኛል፡፡ ሁለቱም ሀገራት እንደተጠበቁት ሁሉ አሳማኝ ብቃት አለማሳየታቸውንም ቢሶከር አመላክቷል፡፡

በውድድሩ በርካታ ሙከራዎችን አድርጎ ግብ ማስቆጠር ያልቻለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የፖርቱጋልን ብሔራዊ ቡድን እየጎዳው ነው የሚሉ ተቺዎች ተነስተውበታል፡፡ ከስሎቬኒያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ያመከነው የፍጹም ቅጣት ምት ደግሞ የሮናልዶን ተቺዎች እንዲበዙ አድርጓቸዋል ይላል ቢ ሶከር፡፡ የፖርቱጋል አሠልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ግን በሮናልዶ ላይ የሚነሱ ትችቶችን አይቀበሉም፤ ኮከቡ አሁንም በከፍተኛ የብቃት ደረጃ ላይ እንዳለ ይናገራሉ፤ ቀዳሚ ምርጫቸውም አድርገው ያሰልፉታል፡፡

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ታላቅ ታሪክ ወደ ጻፈበት ሪያል ማድሪድ ያቀናው ምባፔ እኔም “በማድሪድ ታሪክ እንደምጽፍ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ሮናልዶ በማድሪድ ያደረገው ልዩ ነገር ነው ብሏል፡፡ የሮናልዶን ታላቅነት ማድነቅ እና ማክበር እንደሚፈልግም ተናግሯል፡፡ ምባፔ ስለ ሮናልዶ ሲናገር “በእግር ኳስ ታሪክ ላይ የራሱን አሻራ ጥሏል። ወጣቶችን አነሳስቷል፤ ብዙ ጎሎችን አስቆጥሯል፤ ብዙ ዋንጫዎችንም አሸንፏል። ታሪኩ ለራሱ ይናገራል” ብሏል ፡፡

በሞናኮ ከኪሊያን ምባፔ ጋር የተጫወተው የፖርቱጋል እና የማንቸስተር ሲቲው ኮከብ በርናንዶ ሲሊቫ ኪሊያን ምባፔ ምርጥ ተጨዋች መኾኑን አንስቷል፡፡ ሀገራቸው የምባፔዋን ፈረንሳይ አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍጻሜው እንድታልፍ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ቢቢሲ በዘገባው የፖርቱጋሉ አሠልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ እስካሁን ባሳዩት የተጨዋቾች ምርጫ እየተተቹ ነው ብሏል፡፡

አሠልጣኙም ትችት በሥራ ውስጥ እንደሚያጋጥም ገልጸዋል። ትችቱ ሰዎች ለብሔራዊ ቡድኑ ምን ያህል ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያል ሲሉ አቅለውታል፡፡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተጫዋቾች እና በጣም ፉክክር ያለበት የመልበሻ ክፍል እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ ምሽት 4፡00 ሰዓት ላይ በሐምቡርግ በሚደረገው ጨዋታ የአውሮፓ ዋንጫው ታሪካዊ ተጫዋች ሮናልዶ ወይም የእሱ ተማሪ ምባፔ የጀርመን ቆይታቸው ያበቃል። ይህ እጣ የማን ይኾናል የሚለውም በጉጉት ይጠበቃል።

እስካሁን በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ፈረንሳይ የበላይነቱን ይዛለች፡፡ ከፖርቱጋል ጋር ካደረገቻቸው ያለፉት 14 ጨዋታዎች መካከል 11 ጊዜ በማሸነፍ ትልቅ ክብረ ወሰን አላት፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥታለች፡፡ የተሸነፈችው በአንደኛው ብቻ ነው፡፡ ይሄም በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ነው ይላል የቢቢሲ ዘገባ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here